በመክፈት ላይ

ወቅታዊ

የቤተ ክርስቲያናችንን ወቅታዊ ዜናዎች፣ ቀጣይ መርሐ ግብራት እና መንፈሳዊ ትምህርቶች እዚህ ያገኛሉ።

ወቅታዊ

ወቅታዊ

13 ደቂቃ ንባብ

የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት – ኒቆዲሞስ/Nicodemus

ቅዱስ ያሬድ ንብ የማትቀስመው አበባ እንደሌላት ሁሉን ቀስማ ያማረ የጣፈጠ ማር እንድትሠራ እርሱም ሐዲሳትን ከብሉያት እያስማማ ለጀሮ የሚስማማ ኅሊናን የሚመስጥ ድንቅ ዜማ ባዘጋጀልን መሠረት የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሊቁ “ኒቆዲሞስ ስሙ ዘሖረ ኀቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ ወይቤሎ በጽሚት ረቢ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጽአከ ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻአከ ከመ ትኩን መምሕረ ወበምጽአትከ አብራህከ ለነ ወሰላመ ጸጎከነ አንሥእ ኃይለከ ወነዓ አድኅነነ፤ አስቀድሞ በሌሊት ወደርሱ ይሔድ የነበረ ስሙ ኒቆድሞስ የሚባል ሰው በቀስታ “ሊቅ ሆይ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለው። ኒቆዲሞስም ወደ እርሱ ሔደ፤ ረቢ ኢየሱስንም ሊቅ (አዋቂ) እንደሆንክ ለማስተማር ከአብ ዘንድም እንደመጣህ እኛ እናውቃለን፤ በምጽአትህም አበራህልን፤ ሰላምንም ሰጠኸን፤ ኃይልህን አንሳ፤ መጥተህም አድነን አለው” ይለናል። (ጾመ ድጓ) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር የአይሁድ አለቃ የሚሆን ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው በሌሊት መጣ፤ ስለምን በሌሊት መጣ ቢሉ ከንቱ ውዳሴን ሽቶ አንተ የአይሁድ አለቃ ስትሆን እንዴት ትማራለህ እንዳይባል ሰው በማይመጣበት ከሰው ተለይቶ ሊማር ሽቶ በሌሊት መጣ። እንደዚሁም ምሁረ ኦሪት ነውና ምሥጢር ሊያደላድል ነው። በቀን ጌታን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው ስለነበር ለመጠየቅ አልተመቸውም ነበር፡፡ ጌታም በአእምሮ ያልጎለመሱ ሰዎችን ያስተምር ነበርና በምሳሌ እየመሰለ ያስተምራቸው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ “እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?” እንዲል አጥንት ለመቆርጠም አልደረሱም ነበር። (፩ኛቆሮ.፫፥፩-፫) ኒቆዲሞስ ግን ምሁረ ኦሪት ነውና ጠንከር ያለ ትምህርት ሽቶ በሌሊት መጣ። በተጨማሪም የቀን ልቡና ባካና ነው ኅሊና ይሠረቃልና ክት ሊኅና ሽቶ በሌሊት ሊማር መጣ። አባቶቻችን በሠሩት የትምህርት ሥርዓትም ምንኛ ጥበበኛ እንደ ሆኑ አስተውሉ! በቀን ጆሯችን የአካባቢ ድምጽ ይሰማል፤ ዓይናችን ሌላ ይመለከታል፤ ወጭ ወራጁ አላፊ አግዳሚው ይረብሻል። በሌሊት ግን ኅሊናን የሚሠርቅ ምንም ነገር የለምና ሐሳብን ሰብስቦ ለማስተማር እንዲመች የአብነት ትምህርቱን የሌሊትና የቀን ብለው ከፍለው የቃል ትምህርቱን በሌሊት እንድንማር አደረጉን። የጠቢቡ ሰሎሞን “ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት” የሚለው ቃል ምነኛ ይደንቃል! (መኃ.፫፥፩) ኒቆዲሞስ ነፍሱ የፈለገችውን ሊፈልግ በሌሊት መጣ። ሌሊት ሁሉ ሰው ተኝቶ ባለበት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መቻል እንዴት መታደል ነው። ክርስቲያኖች እስኪ አስቡት! ማንም በሌለበት፣ ሁሉ በተኛበት ሰዓት አልጋችሁ ላይ ሁናችሁ ክርስቶስን መፈለግ በጨለማ ውስጥ ውሳጣዊ ዓይናችሁ ብቻ ተከፍቶ ከአምላካችሁ ጋር መነጋገር እጅግ ልዩ ነውና ሌሊቱን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን አሳልፉት። ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ በመሆኑ ቀን ሥራ ውሎ ሌሊት በእግዚአብሔር ቃል ያርፍ ነበር። ይህ ሐሳብ ለእኛ ዘመንም የሚጠቅም ነውና እንማርበት ዘንድ ወደድኩኝ። ዛሬ የሕዝብ አለቃዎች ሹማምንቶች መኳንንቶች እናንተስ መቼ ነው የምትማሩ? የምትበልጠዋን ጸጋ ታገኟት ዘንድ ያገኛችኋትን ታጸኗት ዘንድ ኑ! የእግዚአብሔር አካል በሆነችዋ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል እየሰማችሁ ዕረፉ። ዛሬ ብዙ ሰው ለምን አትማርም ሲባል ሥራ በዝቶብኝ፣ ቢዚ ሁኜ በማለት መመለሱ እየተለመደ መጥቶአል። እኔ ግን እንዲህ ብዬ እጠይቃችኋለሁ፣ በውኑ የእናንተ ሥራ ከኒቆዲሞስ ይበልጣልን? ወይስ ከዳዊት በላይ ትሠራላችሁ? ወይንስ ከላል ይበላ በላይ ሠርታችሁ ነው? እኔ ግን በመኃልየ መኃልይ እንደ ተጻፈ በምክንያት እየራቃችሁ ነው። “እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፤ የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፤ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ። ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ?” በማለት እንደተናገረችው ሰው የሆን ይመስለኛል። (መኃ.፭፥፪) ይህች ሰው ከረፈደ በኋላ ፍለጋ ብትወጣም ማግኘት ግን አልቻለችም፤ እናም ሁላችንም ዛሬ ሳይረፍድብን ታግለን መጣል ሩጠን መቅደም በምንችልበት ጊዜ ምክንያት በመደርደር አንራቅ ለማለት እወዳለሁ። ኒቆዲሞስ በሌሊት መጥቶ ከጌታችን እግር ሥር ተቀምጦ ሲማር በዓይነ ኅሊናችን እንመልከተው! ግርማ ሌሊቱ ጸብአ አራዊቱ ሳያስፈራው፣ ድካም ሳይበግረው በጌታው እግር ሥር ቁጭ ብሎ ሲማር ቅዱስ ዳዊት ” ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” እንዳለ ከማርና ከሥኳር የሚጣፍጠውን ቃለ እግዚአብሔር ሲሰማ ሰው እንዳያየው ተደብቆ የመጣው ኒቆዲሞስ ከመስቀሉ ሥር የሚገኝ የመከራ ቀን ሐዋርያ ሆነ። (መዝ.፻፲፱፥፻፫-፻፭) ሌሊት በመከራ ይመሰላል፤ በመከራ መጥቶ የተማረው ኒቆዲሞስ ሐዋርያት እንኳን ጥለውት በሸሹ ጊዜ ከመስቀሉ ሥር ተገኘ። ሥጦታ ይሆን ዘንድ የክርስቶስን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር የበቃ ሆነ። ክርስቲያኖች! እናንተስ ክርስቶስን ልትገንዙ ትሻላችሁን? በዚያ በመስቀል ላይ ሳለ ቅድስት ሥጋው ከቅድስት ነፍሱ ሲለይ ከመስቀል አውርዶ የሚቀብረው አጥቶ እናቱ ድንግል ማርያም እያለቀሰች ሳለ የተገኘ የእመ ብርሃንን እንባ ያበሰ ቅዱስ ለመሆን በቃ። አሁንም እንደ ኒቆዲሞስ ሌሊት መጥቶ የሚማር ሰው አጥታ ቤተ ክርስቲያን ስታለቅስ፣ ሰቃልያነ ክርስቶስ ጌታን ዳግመኛ ሊሰቅሉት ሲሹ ከመስቀሉ ሥር የሚገኝ በመከራ የሚጸና ሰው ያስፈልጋልና የዓለም ውጣ ውረድ ሳያግዳችሁ ከቤቱ መጥታችሁ ትማሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። ዛሬ ላይ አንድ ነገር ይደንቀኛል! ሰው ሥልጣን ሲይዝ ከቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውን ሽሽት አስተውሉ! ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ቢሆንም ግን ወደ ጌታ ከመምጣት አላገደውም፤ የዛሬዎቹ አለቃ ግን አለመምጣት ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ሆኖ መታየት እንኳን ያሳፍራቸዋል። የልቤ እምነት እንጅ ማተብ ባላደርግስ በሚል ሐሳብም ማተባቸውን የሚፈቱም አይጠፉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለመመሳሰል ሐብል ያደርጋሉ። ክርስቲያኖች ከአምላካችን በእውነት ወዴት እንሄዳለን? እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት “ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት” እንዲል፤ እንዲህ እያልን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ (ዮሐ ፮፥፷፰) ሊቃውንቱም በቅኔያቸው ረቢ ሰገደ በመንፈቀ ሌሊት ለረቢ አኮኑ አጽባእት እምነ አጽባእት የዓቢ፤ ….. በማለት ጣት ከእጣት እንዲበልጥ የአይሁድ ምሁር የነበረው ኒቆዲሞስ ለጌታችን እንደሰገደ ከቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ በመነሳት ይቀኛሉ። በመጨረሻም ኒቆዲሞስን መምህራችን አድርገን ቀን በሥራችን ስንባክን የምንውል እኛ ማታ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል እንማር ምን አልባት እንደ አካብና ኤልዛቤል የሚያሳድደን ንጉሥ መጥቶ ራብተኞች እንዳንሆን፣ ዛሬ እንቅልፋችንን ቀንሰን ከኃጢአታችንን ነቅተን ቃለ እግዚአብሔር እንብላ ” የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው” (፩ኛነገ.፲፱፥፯) እንዲል፡፡ አምላካችን በቸርነቱ ከእንቅልፋችንና ከኃጢአታችን ነቅተን ቃሉን እንደ ውኃ ተጥተን፣ እንደ ምግብ ተመግበን፣ እንድ መጎናፀፊያ ተጎናጽፈን እንድንኖር ይርዳን። ወስብሐት ለእግዚአብሔርወለወላዲቱ ድንግልወለመስቀሉ ክበር አሜን!!! ምንጭ ፦ ማህበረ ቅዱሳን ድህረገጽ

ወቅታዊ

16 ደቂቃ ንባብ

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት – ገብር ኄር / Faithful Servant

በጎ አገልጋይ ለጌታው ታምኝ እንደመሆኑ ‹‹ገብር ኄር›› ይባላል፡፡ ይህም ስያሜ ለዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት እንደተሰጠ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይገልጻል፡፡ የስያሜው መነሻ የሚገኘው ደግሞ በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው በማቴዎስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት የእገሌና የእገሊት ተብሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የኃላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ሐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡ በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሄዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡ ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው እንዲያተርፉበት ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ኃላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡ ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ኃላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ኃላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት፣ ሁለኃ አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንዲያተርፉበት መክሊቱን ሰጥቷቸው በሄደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሢሰሩ የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ፣ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን እንዳደረገበት ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረና በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው እናነባለን፡፡ በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡ ፩. የአገልጋዮቹ ጌታ ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እንመለከታለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ (ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ እንደከተቱት) ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ትላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፪. በጎ አገልጋዮች በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡ ፫. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ ክፉና ሰነፍ የሆነው አገልጋይ በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሄድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የተለያየ መክሊት መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትእዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡ ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፤ ከሄደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ» በማለት መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ሐሰት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ በትኗልና መሰብሰብም ይገባዋል፡፡ እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፤ ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና መክሊቱን ሲቀበል ከጌታው የተሰጠው ትእዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣትና መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡ በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው ዓይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ4፵ ና ፹ ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡ እግዚአብሔር የልጅነትን ጸጋ በመስጠት ለእኛ ያለውን ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ ልጆች የተባልነው እንዲሁ አይደለም፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውኃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፳፬) ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት እንዲህ በማለት ተናግሯል፤‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› (፩ኛ.ዮሐ.፫-፩) እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ›› (ገላ.፬፥፯) በማለት ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡ ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በዚህም መክሊት እንድንሠራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡ ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በውኂዘ ደሙም ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘለዓለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላካችን በመታዘዝ አቅማችን በሚፈቅደው አገልግሎት ጸንቶ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ በአገልግሎት የመጽናት ምልክቱ ደግሞ አትራፊነት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲደሁም ቅዱሳን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በአትራፊነት ይታወቃሉ፡፡ ለማትረፍ ግን ራሳቸውን ለእውነት ለአገልግሎት ለመከራ አሳልፈው በመስጠት ነው፤ በትንሹ መታመን ሲባል የእኛ አገልግሎት ከፈጣሪ ቸርነት ጋር ስለማይመጣጠን ነው፤ ‹‹በብዙ እሾምሃለሁ›› ማለቱም በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም ከብሮ መኖርን ነው፡፡ ከቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰብአ

ወቅታዊ

25 ደቂቃ ንባብ

የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት – ደብረ ዘይት / Mount Olives

ደበረ ዘይት ትርጉሙ የወራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። ወይም «ደብር» ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ» ማለት ነው። በተገናኝ «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የይወራ ተራራ ማለት ይሆናል። ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ቦታ የሚገኝ ተራራ ሲሆን በመካከል የቄድሮን ሸለቆ ብቻ ነው ያለው። ከግርጌው ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ያረፈበት ወይም የድንግል መካነ መቃብር በዚህ ተራራ ግርጌ ይገኛል። ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምስራቅ ዳገታ ላይ ይገኛሉ። ይህ ተራራ በመፅሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ብዙ ድርጊቶች የተደረጉበት ቦታ ነው። ጌታችን ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ በትንቢት መልክ ተናገረ (ማቴ.24፥3)። በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐረገ (ሉቃ. 24፥50)። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከታማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል። በኋለኛው ምጽ አቱ በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል።(ዘካ. 14፥3–5)። ስያሜው፦ የዓቢይ ጾም እኩሌታ ላይ ያለው ሰንበት በዚህ ተራራ ተጠርቷል። ይህንን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዳግም ምጽአት አድርጎ መዝሙሩን ጽፏል። በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3)። ተብሎ እንደተጻፈው ለደቀ መዛሙርቱ የደግም ምጻቱን፣ የዓለምን ፈጻሜ፣ የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው ስላስተማረ በዓሉ በተራራው ስም ተሰይሟል። የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ከዕለታት አንድ ቀን ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሥነ ሕንፃ በትኩረት እያንዳንዱን ነገር በመመልከት አደነቁ። ጧት በጸሎት ጊዜ ጸሎታቸውን አድረሰው ሲጨርሱ የጧት ፀሐይ አርፎበት ያሸበረቀውን ቤተ መቅደስ ውበቱን አስተውለው ምን ጥበበኛ እንዳሠራው እየተነጋገሩ ጌታችንንም አብሮ እንዲያደንቅ ሲጠብቁ አስደንጋጭ ነገር ተናጋረ። ያ የሚያደንቁት ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፤ አያይዞም ከሞት በኋላ ተነሥቶ እንደሚያረግና ነገር ግን ዓለምን ለማሳለፍ ዳግም እንደሚመጣ ወደፊት የሚሆኑ ሚሥጢራትን እና በቤተ መቅደሱና በሕዝቡ ላይ ሊደርስ ያለውን በትነሹ ጥቆመቸው። ይህም ነገር እረፍት ነሳቸውና ወደ ደብረ ዘይት ከተሻገሩ በኋላ በሰፊው እንዲገልጽላቸው ጠየቁት። ጥያቄውም «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3) የሚል ነው። በዚህ የጥያቄያቸው ክፍል እንደምናየው ጥያቄያቸው ዕለትና ምልክት ነው። ወይም «መቼ» እና «ምን» የሚል ነው። የቤተ መቅደሱ መፍረስ መቼ ይሆናል? የዓለም መጨረሻና የመምጣትህስ ምልክቱ ምንድን ነው? ጌታችንም በቀኙ ያቁመንና ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳይል በጥያቄያቸው ላይ ብቻ አተኩሮ ሰፊ መልስ ሰጥቷቸዋል። መቼ ይሆናል ላሉት የመጀመሪያው ጥያቄ «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም [ሰውም] ቢሆን የሚያውቅ የለም» (ማቴ.24፥.36)። ሲል አጭር መልስ ሲሰጥ።ስለ ሁለተኛው ጥያቄ ስለ ምልክት ጉዳይ ግን መሸከም እስኪያቅታቸው ድረስ አስተምሯቸዋል። በመልሱም ውስጥ ማስጠንቀቂያዎች፣ ምክሮች፣ ማጽናኛዎችና ምሳሌዎች በብዛት ቀርበዋል በተደጋጋሚ ተወስተዋል። ምልክቶቹ፦ 1ኛ/ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ጌታችን በአንደኛ ደረጃ የተናገረው ምልክት በተለያየ ጊዜ በተለያየ ሀገር ብዙ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንደሚነሡ ነው። የጌታ ቃል አይቀርምና ከዚህ ቀደም ብዙ ሰዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ተነሥተው ነበር። ዋናው በዮሐንስ ራእይ ዕራፍ 13 አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የየጥፋት ልጅ» የተባለው ብዙ ጥፋትና መከራ የሚያደርሰው እና በለ 666 መለያ ምልክቱ ሐሳተኛ ክርስቶስ እሲከገለጥ ደረስ መንገድ ጥራጊዎች የሆኑ አለማማጅ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ተነሥተዋል። በእውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚደመሰሰው ሐሳዊ መሲሕ የመጨረሻውና ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚወጋ የታላቁ መከራ ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሆናል። ለዚህ ነው መድኃኒታችን እስኪመጣ ድረስ እናዳንሰናከል አስቀድሞ «ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ … በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ» (ቁጥ. 5 እና 23) ሲል ያስጠነቀቀን። በሀገራችንም በኢትዮጵያ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንገሥት እኔ ክርስቶስ ነኝ የሚል ሐሳዊ/ሐሰተኛ ክርስቶስ ተነሥቶ እንደነበር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ በሀገራችን ተንሥቶ የነበረው ሐሳዊ ክርስቶስ ልክ እንደ እውነተኛው ክርስቶስ 12 ሐዋርያት፣ 72 አርድእትና 36 ቅዱሳት አንስት አስከትሎ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያለ ሲንቀሳቀስ ንጉሡ አስቀርበው አንተ ማን ነህ? ቢሉት በድፍረት እኔ ክርስቶስ ነኝ አላቸው። ንጉሡም ክርስቶስማ ከደንግል ማርያም ተወልዶ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ዓለምን አድኖ ከሞት ተንሥቶ ዐርጓል ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል አንተ ግን ማነህ? ቢሉት አዎ ትክክል ነው። ከዚህ ቀደም ከቤተ እሥራኤል ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልጀ፣ አስተምሬ ተሰቅየ ሙቼ ተነሥቼ ዐርጌ ነበር፤ አሁን ድግሞ ጥቁሮች አፍርካውያን ባይታወር አደረገን እንዳይሉኝ ከእናቴ ከድንግል መርዐተ ወንጌል ለጥቁሮቹ ዳግም ተወልጀ ነው አላቸው። ንጉሡም ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወታል ብለው በሰይፍ አስቀጡት ተካታዮቹም ተበተኑ ይባላል። 2ኛ/ ጦርነት ጦርነት ዱሮም ነበረ። የዚህ ዘመን ጦርነት ግን የበዛና በብዙ ሀገራት የሚካሄድ ነው፣ የዱሮ ጦርነት ሴቶችን፣ አቅመ ደካማ ሺማግሌዎችንና ሕፃናትን ለእልቂት የማያጋልጥ ነበር። የዘመናችን ጦርነት ግን ማንንም የማይለይ ለማንም የማይራራ ሁሉን የሚደፈጥጥ የሁሉን ደም የሚያፈስ አስቃቂነቱ ከመግለጫ ቋንቋ በላይ ሆኖ ይታያል። ይህንንምም ጌታችን የዳግም ምጽ አቱን ምልክት ለጠየቁት ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና» (ቁጥማቴ .6-7) ሲል ተናግሮታል። 3ኛ/ ረሀብ የረሀብ ወሬ ወደ ሌላ ሀገር መሄድ ሳያስፈልገን በገዛ ሀገራችን የምናየው የምንዳሳሰው ያለው ለመርዳት የሌለው ለጸሎት የሚሮጥባት ሀገራችን ኢትዮጵያ አለች። ይህም ሰው ሰራሽ ችግር ለጠላቶቻችን ማሣለቂያ አድርጎን ይኖራል። በተለው የተፈጥሮ ችግር ሳያጋጥማት በሰው ሰራሽ ችግር 8 000 000 ሕዝብ ለአስቸኳ ምግብ ርዳታ የተጋለጠበት ሁኔታ ያሳዝናል። ይህም ዓይነት በጥልና በተንኮል በጭካኔ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የምጽአት ሦስተኛ ምልክት ሆኖ በጌታችን ለደቀ መዛሙርት ተነግሯል «ረሀብም ቸነፈርም በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል» (ማቴ. 24፥7) ተብሎ እንደተጻፈ። 4ኛ/ የምድር መንቀጥቀጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳት በተለያዩ ሀገሮች እንዳደረሰ የሚዘንጋ አይደለም። በ1999፣ ጀምሮ እስከ ዛሬ በተለያዩ ሀገሮች በተለያየ ጊዜ የበዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ አያሌዎችን ቤት ንብረት አልባ ያደረገ የመሬት መቀጥቀጥ ተከሥቷል። በሄይቲ፣ በታይዋን፣ በቱርክ፣ በፊልፕንስ፣ ወዘተ ተከሥቷል። ይህም ለደቀ መዛሙርቱ የዓለም ፍጻሜ ምልክት የማግኘት ጥያቄ የተሰጠው «የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» (ማቴ. 24፥7) ተብሎ በጌታ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ተደርጎ የተነገረው ቃል አይቀርምና እየሆነ ነው። 5ኛ/ የክርስቲያኖች መከራ የክርስቲያኖች መከራ እየጀመረ ይመስላል። ሰይጣን ኢቴስቶችን፣ እስላሞችንና አይሁድን በመጠቀም በክርስቲያኖች ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ችግር መፍጠር የቸመረበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ የክርስቲያኖች ጥያቄ ቶሎ የማይመልስ የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ለማስተናገድም መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶች ፈቃደኛነታችውን እያጡና ይህንን ወንጀላቸውን ለመሸፈንም በሕግ አንቀጽ እየፈጠሩለት ይታያሉ። «በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ» (ማቴ. 24 ቁጥ.9)። ተብሎ እንደተጻፈው ሃይማኖተኛነት እንደ ኋላ ቀርነት ከሐዲነት እንደተራማጂነትና ሥልጡንነት የሚታይበት ዘመን ላይ እንዳለን ግልጽ ነው። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመለካከት ክርስቲያኖችን ወደ ማግለልና ወደ መወንጀል የሚያድግ መሆኑ ከሚታዩት ፍንጮች መረዳት ይቻላል። በእንዲህ አይነት የመከራ ዘመን የክርስቶስ ተቃዋሚዎች በክርስቲያኖች ላይ ከሚያመጡት መከራ የበለጠ የክርስቲያኖች እርስ በእርስ መከዳዳት ጭንቁን ያከፋዋል መከራውን መራራ ያደርገዋል «በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ» (ማቴ.24፥10) ተብሎ በጌታ እንደተነገረ ከሐድያኑ ሆነ ብለው በእቅድ በክርስቲያኖች መካከል መከዳዳትን በመፍጠር ለዚህ ነው ክርስቲአኖች

ወቅታዊ

19 ደቂቃ ንባብ

የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት – መፃጒዕ / infirmity

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መፃጒዕ› ይባላል፡፡ ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል ያለ ነው፡፡ መፃጒዕ ደዌ የጸናበት በሽተኛ፣ ሕመምተኛ ማለት ነው፡፡ መፃጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅ የኖረ ሰው ነው። ስፍራዋም “ቤተ ሳይዳ” ትባላለች።ቤተ ሣህል (የምሕረት ቤት) ማለት ነው፤ መጠመቂያዋም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገብ የምትገኝ ናት፡፡ (ዘሌ.፱፥፪) “ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳና “ቤተ ሳይዳ” ዘገሊላ የሚባሉ እንዳሉ በግልጽ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል። “ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት” …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት” ብሎ ሲገልጽ ነው። (ዮሐ.፭፥፪) ቤተ ሳይዳ ዘኢየሩሳሌም ባለ አምስት በር፣ እርከን (መመላለሻ)፣ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ለማግኘት ጥምቀቱን ሲጠባበቁ የሚኖሩባት ናት። ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ፣ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት እና የአምስቱ መጻሕፍተ ሙሴ ምሳሌ በእነዚያ ተጠብቀው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን፣ እነርሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። አንድም አምስቱ እርከን (መመላለሻ) የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና። አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምእመናን ከእነ ፈተናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እነርሱም አእሩግ በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት በዝሙት፣ አንስት በትውዝፍት (በምንዝር ጌጥ)፣ ካህናት በትዕቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም በአት እየፈቱ በከንቱ የመፈተናቸው ምሳሌ ሆኖ ይነገራል። መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት፣ ነገር ግን በዕለቱ ከአንድ ሕመምተኛ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት። ሐተታው የመጠመቂያ ውኀው የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት (ካህናት) “ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት” የመውረዳቸው ምሳሌ ነው፤ ፈውሱም የሚከናወነው በዕለተ ቀዳሚት ሲሆን የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ የሚድነው አንድ ታማሚ ብቻ መሆኑ የአባቶቻቸው ምሕረት አለመቅረቱን ሲያሳይ፣ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም ድኅነት እንዳልነበረ ያሳያል፡፡ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የኖረ መፃጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ያንን በሽተኛ “ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?” አለው። ማእምረ ኅቡዓት ክርስቶስ፣” አዎን፥ እንዲለው እያወቀ”፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ “የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው አይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። (ዕብ.፬፥፲፪) “ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው?“ እንዲል፤ (መክ.፮፥፲፪) የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ? መፃጉዕ በኋላ የሚክድ ነውና “ሳልፈቅድለት ነው ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ” እንዳይል፣ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። “ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል” በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ውኃው መናወጥ ሳያቆየው “ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር …፤ ተነሥና አልጋህን አንሥተህ ሂድ” አለው፤ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች አልጋ ተሸክሟት ሄደ። ጌታችን መፃጉዕን ‹‹ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው፦ ያለ ተረፈ ደዌ አንሥቶት “ያለህን ይዘህ ሂድ፤ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም” ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ታዲያ ይህ ምስኪን መፃጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ረሳ፤ ማን እንደሆነ እንኳን አላወቀውም። ወንጌላዊውም “ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …፤የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ይለዋል። ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ተዘነጋ። ዛሬም ከደዌው፣ ከማጣቱ፣ ከችግሩ፣ ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ እንደ መፃጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ፣ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው? ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠስ ማን ነው?” (ኤር. ፳፫፥፲፰)። እኛም ብንሆን ከአዳም በደል ነጻ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን የምናፌዝ ሁላችንንም ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል “እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ፡፡” (ኢሳ.፳፰፥፳፪ ) መፃጉዕ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳን አላወቀም። ወንጌላዊውም “የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ብሎ ገልጾታል። (ዮሐ.፭፥፲፫) በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ “ያዳነኝ እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አገኘውና “ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ፤ ከዚህ የከፋ “ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ” እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል” (ቁ.፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ ሰላ ቀርታለች። ዛሬም ቢሆን እንደ መፃጉዕ ሰዎች በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፣ ሰውነታቸው የሰለለ፣ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፣ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን በጠበል ቦታ፣ በገዳማት እና በአድባራት አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መፃጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ። ስለዚህ ይህ ሳምንት ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን ዓቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት ናቸው፡፡ በዚህ ዕለት የእግዚአብሔር አምላካችን ፈዋሽነትና አዳኝነት እንዲሁም ታዳጊነትና የወደቁትን የማይረሳ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑ የሚዘከርበትና ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ቅዱስ ዳዊትም “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፣ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፣ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፣ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት በዝማሬው አረጋግጧል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና” ሲል ሲቀኝ፣ (መዝ.፸፪፥፲፪) ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ “ረዳት (ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡ (ኢዮ.፳፮፥፪) ስለዚህ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ወገን፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ሁል ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ሐሤትም ያድርጉ፡፡ ሁል ጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ” እንዳለው ሁል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች እንሁን። (መዝ.፵፥፲፮) በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መፃጒዕን “ተነሣ” እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሓ እንዲያነሣንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለየን፤ አሜን! በመልእክታቱ የሚነበቡት(ገላ.፭፥፩ እና ያዕ.፭፥፲፬) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ.፫፥፩) የዕለቱ ምስባክ፦ “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሉ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ.፵፥፫) ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል

ወቅታዊ

13 ደቂቃ ንባብ

የዐቢይ ጾም ሶስተኛው ሳምንት – ምኵራብ / Temple

ሦስተኛው ሰንበት “ምኲራብ” ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት “ቦአ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ” ነው፣ ምኩራብ ማለትም ቀጥተኛ ፍችው ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ህንፃ ማለት ነው፣ ከዚህም የተነሣ “የአይሁድ ቤተ ጸሎት ወይም ቤተመቅደስ” ማለት ይሆናል፣ ዐቢይ ፍሬ ቃሉ ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በትምህርቱ፣ ድውያነ ነፍስን በታምራቱ ሲፈውስ በምኩራብ ዮሐንስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 12 እየተገኘ የፈጸመውን የማዳን ሥራ በኀሊና እያሳሰበ የሚያስተምር ሦስተኛ ሳምንት ነው፡፡ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኲራብ ገባ እያለ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሳሳ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኲራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኲራብ የሚሸጡ፣ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ፣ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፣ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ቁጥር 12-13 ተጠቅሷል፡፡ ቆላስያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 16-23 “እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል፣ ወይም ስለ ወር መባቻ፣ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፣ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፣ ትህትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሠሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡ ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት “አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ” ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፣ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን”ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም” ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጧቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ፣ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፣ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሐም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም አብርሐምም እግዚአብሔርን አመነ፣ ፅድቅም ሆኖ ተቆጠረለት ያለው ተፈፀመ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፣ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲፀድቅ ታያላችሁ”፣ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ፣ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ቁጥር 1-9 “በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፣ እርሱም ፅድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ፣ ለህዝብም ብዙ ምፅዋት የሚያደርግ፣ዘወትር ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፣ እግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት “ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው” እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ “ጌታ ሆይ ምንድን ነው? አለ፣ መልአኩም “ጸሎትህና ምፅዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረጓል” አለው፣ አሁንም “ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፣ እርሱ ቤቱ በባህር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጧል፣ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፣ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፣ እነርሱም በነጋታው ሲሄዱ፣ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ፣ መዝሙር ምዕራፍ 68 ቁጥር 9-10 የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና ሰውነቴን በጾም አደከምኳት፣ ስድብንም ሆነብኝ”፡፡ ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ “ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ”፣ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፣ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፣ ዮሐንስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 12 -25 ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፣ ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፣ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፣ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” አላቸው፣ ደቀ መዛሙርቱም “የቤትህ ቅናት ይበላኛል” ተብሎ እንደተፃፈ አሰቡ፡፡ ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት፣ ኢየሱስም መልሶ “ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው” ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት፣ እርሱ ግን “ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር” ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡ በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ “ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” “ወስብሐት ለእግዚአብሔር” ምንጭ ዮሐንስ ንስሐ የቴሌግራም ግሩፕhttps://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

ወቅታዊ

1 ደቂቃ ንባብ

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፲፪ኛ ዓመት በዓለ ሢመት

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፲፪ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል። ዘገባው የተዋህዶ ሚዲያ ማዕከል እና የኢ/ኦ/ተ/ቤ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው ::

ወቅታዊ

10 ደቂቃ ንባብ

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት – ቅድስት / Holy

በዕለቱ የሚነበቡት መልዕክታት የመጀመሪያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች:- ም. 4 ቊ. 1-13 St Paul’s first letter to Thessalonians:- ch. 4 nu. 1-13 የጳውሎስ መልዕክት ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች የመጀመሪያው:- ም. 4 ቊ. 1-131፤ እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን።2፤ በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና።3፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤4-5፤ ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤6፤ አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል።7፤ ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።8፤ እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ።9፤ እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤10-12፤ እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።13፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። English1. Furthermore then we beseech you, brethren, and exhort you by the Lord Jesus, that as ye have received of us how ye ought to walk and to please God, so ye would abound more and more.2. For ye know what commandments we gave you by the Lord Jesus.3. For this is the will of God, even your sanctification, that ye should abstain from fornication:4. That every one of you should know how to possess his vessel in sanctification and honour;5. Not in the lust of concupiscence, even as the Gentiles which know not God:6. That no man go beyond and defraud his brother in any matter: because that the Lord is the avenger of all such, as we also have forewarned you and testified.7. For God hath not called us unto uncleanness, but unto holiness.8. He therefore that despiseth, despiseth not man, but God, who hath also given unto us his holy Spirit.9. But as touching brotherly love ye need not that I write unto you: for ye yourselves are taught of God to love one another.10. And indeed ye do it toward all the brethren which are in all Macedonia: but we beseech you, brethren, that ye increase more and more;11. And that ye study to be quiet, and to do your own business, and to work with your own hands, as we commanded you;12. That ye may walk honestly toward them that are without, and that ye may have lack of nothing.13. But I would not have you to be ignorant, brethren, concerning them which are asleep, that ye sorrow not, even as others which have no hope. Close የመጀመሪያው የጴጥሮስ መልዕክት:- ም. 1 ቊ. 13-ፍ.ም St Peter’s first letter:- ch. 1 nu. 13-end 13፤ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።14፤ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።15-16፤ ዳሩ ግን፦ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ፡” ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።17፤ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ።18-19፤ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።20-21፤ ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።22፤ ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።23፤ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።24፤ ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤25፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።English St Peter’s first letter:- ch. 1 nu. 13-end13. Wherefore gird up the loins of your mind, be sober, and hope to the end for the grace that is to be brought unto you at the revelation of Jesus Christ;14. As obedient children, not fashioning yourselves according to the former lusts in your ignorance:15. But as he which hath called you is holy, so be ye holy in all manner of conversation;16. Because it is written, Be ye holy; for I am holy.17. And if ye call on the Father, who without respect of persons judgeth according to every man’s work, pass the time of your sojourning here in fear:18. Forasmuch as ye know that ye were not redeemed with corruptible things, as silver and gold, from your vain conversation received by tradition from your fathers;19. But with the precious blood of Christ, as of a lamb without blemish and without spot:20. Who verily was foreordained before the foundation of the world, but was manifest in these last times for you,21. Who by him do believe in God, that raised him up from the dead, and gave him glory; that your faith and hope might be in God.22. Seeing ye have purified your souls in obeying the truth through the Spirit unto unfeigned love of the brethren, see that ye love one another with a pure heart fervently:23. Being born again, not of corruptible seed, but of incorruptible, by the word of God, which liveth and abideth for ever.24. For all flesh is as grass, and all the glory of man as the flower of grass. The grass withereth, and the flower thereof falleth away:25. But the word of the Lord endureth for ever. And this is the word which by the gospel is preached unto you. Close የሐዋርያት ሥራ:- ም. 10 ቊ. 17-30 Acts of The Apostles:- ch. 10 nu. 17-30 17፤ ጴጥሮስም ስላየው ራእይ፦ “ምን ይሆን?” ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤18፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፦ “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን?” ብለው ይጠይቁ ነበር።19፤ ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ፦ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤20፤ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፡” አለው።21፤ ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ፦ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር

ወቅታዊ

1 ደቂቃ ንባብ

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለደብራችን ዋና ጸሐፊ ሊቀ ሥዩማን ዳግማዊ ወርቁ የቅስና ሥልጣነ ክህነት ሰጡ!

እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ የደብራችን መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ሊቀ ሥዩማን ዳግማዊ ወርቁ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በብፁዕነታቸው አንብሮተ ዕድ የቅስና ሥልጣነ ክህነትን ተቀብለዋል።የደብራችን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለሊቀ ሥዩማን ቀሲስ ዳግማዊ ወርቁ መልካም የአገልግሎት ዘመንን ይመኛል።

ወቅታዊ

1 ደቂቃ ንባብ

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ለ312 ደቀ መዛሙርት ሥልጣነ ሰጡ፡፡

በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በሰበታ እና ገላን ክፍላተ ከተማ ሥር በሚተዳደረው በዓለም ገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከተለያዩ ገዳማት እና አድባራት ለተውጣጡ 270 ደቀ መዛሙርት ሥልጣነ ዲቁና ለ38 ዲያቆናት የቅስና እንዲሁም ለ4 አባቶች የቁምስና ሥልጣነ ክህነት ተሰጥቷል፡፡ በዕለቱ ለደቀ መዛሙርቱ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በሚመቻችሁም በማይመቻችሁም ሁሉ ድሀ ሀብታም ሳትሉ ሁሉን በአግባቡ እና በሥርዓቱ ማገልገል ይጠበቅባችዋል ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም ይህ ሥልጣን ለማንም ያልተሰጠ ሰማያዊ ሥልጣን ነውና ዛሬ የተሾማችሁ ሁሉ በብርታት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተጋችሁ ሁኑ ሲሉ አሳስበዋል ሲል የዘገበው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት