Loading

News & Updates

Church news, upcoming programmes and spiritual teaching, all in one place.

News & Updates

Current News

1 min read

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ለ312 ደቀ መዛሙርት ሥልጣነ ሰጡ፡፡

በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በሰበታ እና ገላን ክፍላተ ከተማ ሥር በሚተዳደረው በዓለም ገና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከተለያዩ ገዳማት እና አድባራት ለተውጣጡ 270 ደቀ መዛሙርት ሥልጣነ ዲቁና ለ38 ዲያቆናት የቅስና እንዲሁም ለ4 አባቶች የቁምስና ሥልጣነ ክህነት ተሰጥቷል፡፡ በዕለቱ ለደቀ መዛሙርቱ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በሚመቻችሁም በማይመቻችሁም ሁሉ ድሀ ሀብታም ሳትሉ ሁሉን በአግባቡ እና በሥርዓቱ ማገልገል ይጠበቅባችዋል ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም ይህ ሥልጣን ለማንም ያልተሰጠ ሰማያዊ ሥልጣን ነውና ዛሬ የተሾማችሁ ሁሉ በብርታት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተጋችሁ ሁኑ ሲሉ አሳስበዋል ሲል የዘገበው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት

Current News

2 min read

ታላቅ የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ

የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት መጠናቀቁን አስመልክቶ፤ በዛሬው ዕለት በደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ በዓመቱ የተሠሩት ሥራዎች እና የተገኘው አመርቂ ውጤት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን ለብፁዕነታቸው እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ መስተዳደር ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና ቀርቧል። በተያያዘም በክፍለ ከተማው የሚገኙ አድባራት እርስ በእርስ ተግባብተውና ተነጋግረው ስለሚሠሩ የሚሰጠው አገልግሎት እየሰፋ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ፣ ለምእመኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ቤተ እምነቶች ጭምር ወደ ክርስትና መመለስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተገልጿል። በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ፣ የጠቅላይ ቤ/ክ እና የአ/አ/ሀ/ ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም በክፍለ ከተማው ስር ባሉ አድባራትና ገዳማት የሚያገለግሉ አስተዳዳሪዎች፣ፀሓፍት፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት፣ የሂሳብ ሹሞች፣ቁጥጥሮች፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል። ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ፍሬ ጻማከ ተሴሰይ ብፁዕ አንተ ወሰናይ ለከ ። መዝ 128፥2” ላይ የሚገኘውን ኃይለ ቃል በማንሳት የተዘጋጀውን የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር በማመስገን “ይህ ሽልማትና ዕውቅና የሚገባው የአዝመራው የእሸቱ ፍሬ ለሆኑት ዓመቱን ሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ማኅሌቱን ፣ ሰዓታቱን ያለማቋረጥ ሲያገለግሉ ለነበሩ ሊቃውንት ፣ ካህናት ነው ።” በመቀጠልም ምእመናን በሰላም አገልግሎት እንዲያገኙ ላስቻሉ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን ፣ በክፍለ ከተማው ስለሚታየው የስብከተ ወንጌል መስፋፋት ፣ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሠ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅን አመሥግነዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም በሀገረ ስብከቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉንም ሠራተኛ በማሰልጠን የማብቃት ሥራ መሠራት እንዳለበት አንስተው ሥልጠናዎች ከሀገረ ስብከት እስከ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በማሳሰብ በቀጣዩ ዓመት ሁሉም አገልጋይ ቤተ ክርስቲያን የጣለችበትን ኃላፊነት አጠናክሮ መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል። የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው በዚህ ዓመት የሰበካ ጉባኤ ሕግን የማወቅና የማስፈጸም ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ይዞታ የማስፋፋት ፣ ያሉትን ይዞታ የማስጠበቅ ሁኔታ የታየበት ነው ፤ ይሄ ሁሉ ስኬት የተገኘው ሥራው የሀገረ ስብከቱ ብቻ ነው ሳይሉ በራሳቸው ጥረት ብዙ በመሥራታቸው ነው ፤ ይሄ ሽልማት በቀጣይ የተሻለ እንዲሠሩ ማበረታቻ ይሆናል ባማለት መርሐ ግብሩን ያዘጋጁ ባለ ድርሻ አካላትን አመሥግነዋል። የሽልማት ሒደቱን በተመለከተ በተለያየ መስፈርት እና የሥራ አፈጻጸም ደረጃ በደረጃ የተቀመጡ መሆናቸው በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሠ የተገለጸ ሲሆን ፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ፣ ለሌሎች አድባራት ደግሞ የምስክር ወረቀት ፣ አዲስ ተቋቁመው እያገለገሉ ላሉ አብያተ ክርስቲያናትም የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል። በልዩነት ደግሞ ለአድባራቱ አስተዳዳሪዎችና ሊቃነ መናብርት የምስጋና መርሐ ግብር ተደርጎ ተጠናቋል። ምንጭ ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል

Current News

9 min read

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን በውግዘት ተለይተው የነበሩትን የዐሥራ ሰባቱ አባቶች ውግዘት ማንሳቱን በመግለጫው አሳወቀ።

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ክህነት ውጭ በሆነ መንገድ በራሳቸው ሥልጣንና በይገባናል ስሞታ የኦሮሚያ ሲኖዶስ መሥርተናል በሚል ተልእኮ ሲንቀሳቀሱ ቢቆዮም በይቅርታ መመለሳቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ይህን ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ከመጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ የሦስቱን አባቶችና የሃያዎቹን መነኮሳት ውግዘት ቅዱስ ሲኖዶሱ ማንሣቱ የታወቀ ሲሆን ውግዘቱ የተነሳላቸውም አባቶች ቀድሞ ቤተ ክርስቲያን በሰጠቻቸው ማዕረግ እንደሚጠሩም ገልጿል። በመሆኑም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ተብለው እንደሚጠሩ እንዲሁም ወደ ነበሩበት አገልሎታቸው እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሃያዎቹ መነኮሳትም አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያን በሰጠቻቸው ስም እና አገልግሎት እንዲያገለግሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል። የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚከተለው ነው፡፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!! ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሕገወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተከናወነው ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖና አስተዳደራዊ መዋቅር የጣሰ ሕገወጥ አድራጎት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በመወያየት ሕገወጡን ሹመት ያከናወኑትና ተሿሚዎችን በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት ከዲቁና ጀምሮ የነበራቸውን ማዕረገ ክህነት በሙሉ በመሻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባልነት አውግዞ መለየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ምንም እንኳን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በውሳኔው ውግዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በድርጊታቸው ተጸጽተው እና ከስህተታቸው ተመልሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት የሚሰጣቸውን ቀኖና ተቀብሎ ለመመለስ ዝግጁ ከሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የይቅርታ በር ክፍት መሆኑን በማሳወቅ መግለጫ የሰጠ ቢሆንም ግለሰቦቹ ከስህተታቸው ተምረው በይቅርታ እድሉ ከመጠቀም ይልቅ በሕገወጥ መንገዱ ቀጥለውና ውግዘቱን ጥሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው በሚያገለግሉባቸው አህጉረ ስብከት ላይ እርስ በርሳቸው በመመዳደብ እያደረጉት የነበረውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ መንግስት በሕግ የተጠላበትን ሕግን የማስከበር ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያናችንን ተቋማዊ ልዕልና እንዲያስከብርልን ከመግለጫም አልፎ በደብዳቤ ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አጥቶ በሕገወጥ መንገድ የተሾሙት ግለሰቦች በመንግሥታዊ የፀጥታ አካላት ታጅበው በኦሮምያ ክልል የሚገኙትን አህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በኃይል ሰብረው ተቋማቱን በመውረር ሀብትና ንብረት የተዘረፈ ሲሆን ይህም ሕገወጥ ድርጊት በሚከናወንበት ወቅት ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን አይጣስም፣ ሲኖዶሳችን አይከፈልም፣ ቀኖናችን አይደፈርም በማለት በጽናትና በአንድነት ድርጊቱን የተቃወሙት ምዕመናን፣ ወጣቶችና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ የሥራ ኃፊዎች በተለይም የሻሸመኔና አካባቢው ምእመናንና አገልጋይ ካህናት ለሞት፣ ለአካልና የሞራል ጉዳት፣ ለእስራትና እንግልት ተዳርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን እና ፈተናውን የማሳለፍ ሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በምሕረት አይኑ ተመልክቶ የመጣውን ፈተና ያስወግድልን ዘንድ በጾመ ነነዌ ለሦስት ቀናት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ተከታዮች ማቅ ለብሰው በጸሎትና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እንዲያመለክቱ በወሰነው መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ተፈጽሞ በማያውቅ ሁኔታ እንኳንስ ልጆቿ ምእመናን ይቅርና እራሷ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የሀዘን መገለጫ የሆነውን ጥቁር ማቅ ለብሳ ከሀገር አቀፍም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀዘኗን ገልጣለች፡፡ የእናት ቤተ ክርስቲያንና የልጆቿ ምዕመናን እንባና ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ለውይይት ዝግ የነበረው የመንግስታችን በር ለውይይት ተከፍቷል፡፡ የደረሠብን የጉዳት ከፍተኛነት በሀገራችን መንግሥታዊ ሚዲያዎች ዘንድ ቦታ ቢያጣም አለም አቀፍ ሚዲያዎችና የቤተ ክርስቲያናችን የሚዲያ ተቋማት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲደርስ በማድረጋቸው ችግሩን ከእኛም አልፎ በሁሉም አኃት አብያተ ክርስቲያናት፣ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች ሲቢክ ማህበራት ድርጊቱን በማውገዝ ለእናት ቤተ ክርስቲያናችን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ በዚህም በችግራችን ወቅት ከጎናችን ለቆሙት አካላት በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም በድጋሚ ከፍ ያለ ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡ በመጠቀልም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባመቻቹት የውይይት መድረክ በተወከሉ ብፁዓን አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በኩል በተደረገው መጠነ ሰፊ ውይይት መሠረት ባለ ዐሥር ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት በተደረሰው መሠረት ሦስቱ የቀድሞ አባቶች የካቲት ፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ መጥተው በቀድሞ በዓታቸው ተወስነው እስካሁን የቆዩ ሲሆን ሃያዎቹ ተሿሟዎች ደግሞ በስምምነቱ መሠረት ለውሳኔው ተገዥ መሆናቸውን በመግለጽ መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት መሠረት ውግዘቱ እንዴት ሊፈታ እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱን የቀኖና ቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢ በማድረግ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን እንደሚከተለው በአጭሩ ተገልጿል፡፡ ሀ. “ኢይክል ሰብእ ነሢአ ፀጋ ለሊሁ ወኢምንተኒ እመ ኢተውህበ ሎቱ እምሰማይ” ሰው ከእግዚአብሔር ካልተሰጠው በስተቀር እርሱ ራሱ ጸጋን ገንዘብ ማድረግ አይችልም” (ዮሐ.፫፥፳፯) በማለት በቅዱስ ወንጌል እንደተነገረው የእግዚአብሔር ጸጋ ከላይ የሚሰጠው በቅንነት፣ በትሕትና፣ በትዕግሥትና በጸሎት በመሳሰለው እንጅ በሥርዓተ አልበኝነትና በሕገወጥ የድፍረት መንገድ የሚገኝ የእግዚአብሔር ጸጋ የለም፤ አልኖርም፤ አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ለ. ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር በከመ አሮን” እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብርን ለራሱ የሚወስድ የለም ሲል ክብረ ክህነትን በሚገባ ገልጿል፡፡ (ዕብ.፭፥፬) እንዲህም በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭና ቅዱስ ፓትርያርኩ በሌሉበት በድብቅ የተፈጸመው ሕገወጥ ሢመተ ክህነት ለሿሚውም ሆነ ለተሿሚው የእግዚአብሔርን ጸጋ በራስ ፈቃድ እንደመውሰድ ስለሚቆጠር ከፍተኛ የሆነ የዶግማ ጥሰት ተግባር ነው፡፡ ሐ. ከቅዱስ ቃሉ እንደተማርነው “ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሀ እግዚአብሔር፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (መዝ.፻፱፥፲፣ ምሳ.፩፥፯) ይህንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት በማድረግ “ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ስገዱ” (መዝ.፳፰፥፪)፣ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ” (መዝ.፪፥፲፩)፣ “ንትነሣእ በፍርሃተ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔርን በመፍራት እንነሣ (ቅዳ.ማ)” በማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እስከ እስትንፋሰ ደኃሪት መልእክቷን ዘወትር ታስተላልፋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመው ድርጊት ግን በከፍተኛ ድፍረትና በሕገወጥ መንገድ ከመፈጸሙና የሥልጣነ ክህነትን ክብር ከማጉደፉም በላይ ከውግዘትም በኋላ ከጥፋቱ ባለመማር ሕገወጥነትን እንደ ሕጋዊነት፣ ጥፋትን እንደ ልማት፣ ሐሰትን እንደ እውነት፣ የነፍስ ጥፋትን እንደ ነፍስ ማዳን ተቆጥሮ በልበሙሉነት የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አበያተ ክርስቲያናት በር በኃይል ተሰብሮ የመውረር ሕገወጥ ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ይህም ድርጊት ከውግዘት በኋላ በመሆኑ ሕገ እግዚአብሔርን እያወቁ ወደጎን በመተው የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ የዶግማ ጥሰት ነው፡፡ መ. ቅዱሳን ሐዋርያት ከወሰኗቸው የሕግጋት መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ አንድ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ “ወአዘዝነ ከመዝ መዓርገ ሢመታት ለቤተ ክርስቲያን በአርአያ ዘበሰማያት የቤተ ክርስቲያናችን የሹመቶች መዓርግ በሰማያት ባለው አምሳል እንዲሆን አዘዝን” በማለት በንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ “ወንሕነ ንጌሥጽክሙ ከመ ይንበር ኲሉ ለለ አሐዱ አሐዱ እምኔክሙ ውስተ ዘተጸውዐ እምኀበ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ – ከእናንተ ሁሉ እያንዳንዱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በተጠራበት ተልእኮ ጸንቶ ይኖር ዘንድ እኛ እንመክራችኋለን በማለት እያንዳንዱ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ፀጋና ተልእኮ ጸንቶ ከሚኖር በቀር ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ባልተሰጠውና ባልተፈቀደለት በሕገወጥ መንገድ ሊሾምም ሆነ ሊሾም እንደማይገባው የሚያስተምረን አምላካዊ ቃል ነው፡፡ ሠ. ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ ፳ ላይ “በእንተ ዘይሰየም በህልያን እመሂ ኤጲስ ቆጶስ አው ቀሲስ አው ዲያቆን ዘይእኀዝ መዓርገ ሢመት በሕልያን ይሰአር፤ ወይሰዐር ዘሤሞሂ ወይትመተር ለዝሉፉ እምሥርዐተ ክህነት፤ ወኢይሳተፍዎ ወኢበምንትኒ በከመ ረሰይክዎ ለሲሞን መሠርይ እምኀቤየ አነ ጴጥሮስ – መማለጃ በመስጠት ስለሚሾም ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሹመት መዓርግ ቢይዝ ይሻር፣ የሾመውም ይሻር ከክህነት ሥርዓትም እስከ መጨረሻው ይባረር፡፡ እኔ ጴጥሮስ ጠንቋዩ ሊሞንን እንዳደረግሁት በምንም ነገር አያሳትፉት (ሲኖ.ዘሐዋ.ክፍል ሦስት ቁጥር ፳) በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ሥልጣነ ክህነትን ያለአግባብ የሰጠም ሆነ የተቀበለ

Current News

3 min read

ዜና ዕረፍት

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት እና የውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የድሬዳዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል። ብፁዕነታቸው ለረጅም ጊዜ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል። በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ከ፲፬ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል አንዱ ሆነው ከተሾሙበት ከሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ በአገልግሎት ኖረው በመጋቢት ፲፪፣፳፻፲፭ ዓ.ም እንዳረፉ መዝገበ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ የብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ የሕይወት ታሪክ ውልደት የቀድሞው አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የኋላው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ከአባታቸው ከሊቀ መዘምር መለስ አየነው ደስታና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፀሐይ ገብረ አብ በሰሜን ጎንደር ደብረ ሰላም ሎዛ ማርያም አካባቢ በ1፲፱፻፷፩ ዓ.ም ተወለዱ። ትምህርት ቋንቋ መዐርገ_ክህነት አገልግሎት «በጎ ነገር የሆነው ሁሉ ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ፍጻሜ ሊያገኝ አይችልም ተብሎ በተጻፈው መሠረት ምንም እንኳን ሁሉም ተመራጮች ቆሞሳት ከዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸው ጋር የድምፅ ብልጫ በማግኘት ሊመረጡ የቻሉት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መሆኑ ቢታመንበትም ቅሉ ቆሞስ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ግን ከእጩ ተወዳዳሪያቸው ጋር እኩል ድምፅ አግኝተው የተመረጠት በዕጣ ስለሆነ በእሳቸው ምርጫ በይበልጥ እደ መንፈስ ቅዱስ እንዳለበት ያሳያል፡፡ የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን::

Current News

3 min read

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡ ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት እና መንፈሳዊ ዕድገት ትኩረት በመስጠት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በዚሁ መሠረት፡- ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ጉልላት እንደመሆኗ ሰላም መሠረታዊ ተልእኮዋ ነው፡፡ ስለዚህ ወቅታዊውን ችግር ታሳቢ በማድረግ በመላው አገራችን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ተቋማት ጋራ የሚሠራ፣ በሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚኖረው የሰላም ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡ በትግራይ ክልል በሚገኙት አህጉረ ስብከት ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ልዑክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ተልእኮውን እንዲፈጽም ምልዓተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ ወገኖቻችን ያሉበትን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ በማድረግ አስቸኳይ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ በወቅታዊ ችግር ምክንያት በመላው ሀገራችን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ በአጠቃላይ ችግሮቹን በጥናት በመለየት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ልጆቿን በማስተባበር ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ የማጽናናትና የመጎብኘት መርሐ-ግብሮች እንዲደረጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ መቀሌ የሚገኘው የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሠራተኞችን ደመወዝና የሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲለቀቅና በ፳፻፲፮ በጀት ዓመት ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የሆነ የመማር ማስተማሩ የሥራ ሂደት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጪው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግብ መሪ ዕቅድ በማጽደቅ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅሮች ተግባራዊ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ቀደምት አበው በቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም ገዳማት እንዲስፋፉ ሁሉ የነሱን አሰረ ፍኖት በመከተል በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ካልፎርኒያ ግዛት የተቋቋመው ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም እንዲጠናከር፤ በተጨማሪም በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የአስተዳደር፣ የጽሙና፣ የትምህርትና የምርምር ማዕከል እንዲመሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአህጉረ ስብከትና በአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት ስለተቋረጠ፣ በርካታ ምእመናንና ካህናት በእስርና እንግልት ላይ ስለሚገኙ በዚሁ መነሻነት ችግሮች እንዲቀረፉና ወደ መደበኛው የአሠራር መዋቅር እንዲመለስ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን በመሠየም ከፌዴራልና ከኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የመንፈሳዊ ኮሌጆች መከፈት እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር በተመለከተ በኢሉ አባቦራ የመቱ ፈለገ ሕይወት የነገረ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲከፈት የተፈቀደ ሲሆን በሌሎች አህጉረ ስብከት ሊከፈቱ የታሰቡ ኮሌጆችን እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን መሠረታዊ ጥናት ተደርጎ ለ፳፻፲፮ ዓ.ም. የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ ክፍት በሆኑና በተደራቢነት በተያዙ፣ ጉልህና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው በኦሮምያ ክልልና በደቡብ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከት ላይ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡ ወደፊትም ተደርበው በተያዙና አስፈላጊ በሆኑ አህጉረ ስብከት እንደአስፈላጊነቱ በመንበረ ፓትርያርክ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ በመጨረሻም በሀገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩትን አላስፈላጊ ግጭቶች የዜጐች መፈናቀል፣ ስደት ተወግዶ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ በእኩልነት፣ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ በአንድነት እንዲኖር፤ ለማድረግ ግጭቶችና አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡ እንዲሁም በመላው ዓለም ጦርነት ባለባቸው ሀገራት ሁሉ ሰላም እና ዕርቅ እንዲሰፍን በመመኘት እና በመጸለይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ድረስ ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ! ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን! አባ ማትያስ ቀዳማዊፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ምአዲስ አበባኢትዮጵያ

Current News

1 min read

የዩኬና አየርላንድ ማኀበረ ካህናት ጥንታዊ ቅርሶቻችንን አስመለሰ።

የዩኬና አየርላንድ ማህበረ ካህናት ከሀገራችን በህገ-ወጥ መንገድ መውጣቱ የተነገረለትን ረዥም ዓመታት ያስቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንን ነዋየ ቅዳሳት ከእንግሊዝ ሀገር አስመለሰ። በርክክቡ ወቅት የተገኙት የዩኬና አየርላንድ ማኀበረ ካህናት ዋና ሰብሳቢ መጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ሚካኤል ለቅርሱ መመለስ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን አካላት በማመስገን የዩኬና አየርላንድ ማኀበረ ካህናት በተለይ በዪኬና አየርላንድ በጀመራቸዉ መጠነ ሰፊ ቤተክርስቲያንን የማስተዋወቅ እና ቅርሶቻችንን የማስመለስ እንቅስቃሴ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡ ቅርሶች በእንግሊዝ፣ ጣልያንና ፈረንሳይ በስፋት እንዳሏት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተያያዘ ዜናም በዕለቱ በተካሄደው በዩኬ የሃይማኖቶች ኀብረት ጉባኤ ላይ ማኀበራችን የተሳተፈ ሲሆን ስለ ዩኬና አየርላንድ ማህበረ ካህናት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልግሉት በዩኬ እና አየርላንድ አጠቃላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተደርጓል። የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉhttps://youtube.com/channel/UCYUkIT_TcBYzR12SgxV2YHAአጫጭር ትምህርታዊ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት ፌስቡካችንን ይመልከቱ።https://www.facebook.com/mahibere.kahinatuk.5

Current News

1 min read

የእህታችን አዜብ የፍትሀትና የሀገር ቤት ሽኝት ስርዓት በእግዚአብሄር ፍቃድ በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል

ሰላም ይሁን ለሁላችሁም ይህ ድንግተኛ ክስተት እንደ ኮሚኒቲ አደናግጦን ነበር:: ሆኖም በናንተው ቅንና በጎ ትብብር የእህታች የአስክሬን ሽኝት በተሳካ ሁኔታ እውን ሊሆን ችሏል። ለዚህ ስኬት ህብረተሰቡን ከተለያየ ቦታ በማስተባበር እና ገንዘብ በመሰብሰብ የረዱንን እንደሚከተለው እናቀርባለን: 1- በሊቀ ትጉሃን ብርሃኑ እስተባባሪነት ከሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን: ከሊቨርፑል ከኤርትራ ቅዱስ ኡራኤል: ሊድስ መድሃኔ አለም: ሼፌልድ ቅዱስ ሚካኤል በድምሩ £4670.67 2- የማንችስተር ደብረ ሰላም ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን £1225 3-በጎፈንድሚ የተስበስበ ከአገልግሎት ክፍያ ውጪ £1973 4-ከለንደን በሳራ በኩል የተገኝ የድሬ ልጆች £1800 5- ከሟች አዜብ ቤት የተገኘ £200 6- የማንችስተር ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን £391.29 7- የስላሴ ማህበረተኞች £200 8- ለእኔ በግል የተሰጠ £110 በድምሩ ባጠቃላይ £10,569.96 ማሰባሰብ ተችሏል ከዚህ ውስጥ ለአስክሬን ዝግጅትና ወደ ሀገር ቤት እስክ ድሬደዋ የማጏጏዣ ክፍያ £5540 እንዲሁም አገር ቤት ለምትገኘው የአዜብ ልጅ ( ኦፊሺያል ተወካይ)£1000 ወጪ ተደርጏ ተልኳል:: በቀጣይም ቀሪው £4029.96 ለመላክ ዝግጅት አድርገናል:: በመጨረሻ ከሩቅም ከቅርብም የእህታችን አዜብን ህልፈት ሰምታችሁ ሞተ እረፍቷ በሀገሯ እንዲፈፀም ለተባበራችሁ ሁሉ በግሬተር ማንቸስተር የኢትዬጵያ ኮሚዬኒቲ ስም ልባዊ ምስጋናችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ ከሰላምታ ጋር ታምሩ ሰይፉበግሬተር ማንቸስተር የኢትዬጵያ ኮሚዬኒቲሊቀ መንበር

Upcoming Programmes

1 min read

ቀጣይ መርሃግብር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን ክርስቶስ ተንስአ እሙታን : በዐቢይ ኃይል ወስልጣንአሠሮ ለሰይጣን : አግዐዞ ለአዳምሰላም : እምይእዜሰኮነ : ፍስሃ ወሰላም እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ (በዓለ መንፈስ ቅዱስ) በሰላም በጤና በፍቅር አደረሳችሁ፤ አደረሰን:: የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአደራ ልጆች የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወዳጆች ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በቀን 03/06/2023 ቅዳሜ በጧቱ 6:30 am በሊቨርፑል መካነ ቅዱሣን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የቅዳሴ መርሃ ግብራችን ስለሆነ፣ ሁላችንም በሰዓቱ ተገኝተን የቅዳሴው በረከት ተካፋዮች እንድንሆን ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች። ለሌሎችም እንዲደርስ አጋሩ። ለሀገራችን ብሎም ለቤተክርስቲያናችን ፍፁም ሰላምን ፍቅር አንድነትን ይስጥልን ይጠብቅልን።