Loading

ታላቅ የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ

ታላቅ የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ

This post is only available in Amharic.

የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት መጠናቀቁን አስመልክቶ፤ በዛሬው ዕለት በደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ በዓመቱ የተሠሩት ሥራዎች እና የተገኘው አመርቂ ውጤት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን ለብፁዕነታቸው እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ መስተዳደር ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና ቀርቧል። በተያያዘም በክፍለ ከተማው የሚገኙ አድባራት እርስ በእርስ ተግባብተውና ተነጋግረው ስለሚሠሩ የሚሰጠው አገልግሎት እየሰፋ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ፣ ለምእመኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ቤተ እምነቶች ጭምር ወደ ክርስትና መመለስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተገልጿል።

በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ፣ የጠቅላይ ቤ/ክ እና የአ/አ/ሀ/ ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም በክፍለ ከተማው ስር ባሉ አድባራትና ገዳማት የሚያገለግሉ አስተዳዳሪዎች፣ፀሓፍት፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት፣ የሂሳብ ሹሞች፣ቁጥጥሮች፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ፍሬ ጻማከ ተሴሰይ ብፁዕ አንተ ወሰናይ ለከ ። መዝ 128፥2” ላይ የሚገኘውን ኃይለ ቃል በማንሳት የተዘጋጀውን የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር በማመስገን “ይህ ሽልማትና ዕውቅና የሚገባው የአዝመራው የእሸቱ ፍሬ ለሆኑት ዓመቱን ሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ማኅሌቱን ፣ ሰዓታቱን ያለማቋረጥ ሲያገለግሉ ለነበሩ ሊቃውንት ፣ ካህናት ነው ።” በመቀጠልም ምእመናን በሰላም አገልግሎት እንዲያገኙ ላስቻሉ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን ፣ በክፍለ ከተማው ስለሚታየው የስብከተ ወንጌል መስፋፋት ፣ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሠ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅን አመሥግነዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም በሀገረ ስብከቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉንም ሠራተኛ በማሰልጠን የማብቃት ሥራ መሠራት እንዳለበት አንስተው ሥልጠናዎች ከሀገረ ስብከት እስከ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በማሳሰብ በቀጣዩ ዓመት ሁሉም አገልጋይ ቤተ ክርስቲያን የጣለችበትን ኃላፊነት አጠናክሮ መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው በዚህ ዓመት የሰበካ ጉባኤ ሕግን የማወቅና የማስፈጸም ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ይዞታ የማስፋፋት ፣ ያሉትን ይዞታ የማስጠበቅ ሁኔታ የታየበት ነው ፤ ይሄ ሁሉ ስኬት የተገኘው ሥራው የሀገረ ስብከቱ ብቻ ነው ሳይሉ በራሳቸው ጥረት ብዙ በመሥራታቸው ነው ፤ ይሄ ሽልማት በቀጣይ የተሻለ እንዲሠሩ ማበረታቻ ይሆናል ባማለት መርሐ ግብሩን ያዘጋጁ ባለ ድርሻ አካላትን አመሥግነዋል።

የሽልማት ሒደቱን በተመለከተ በተለያየ መስፈርት እና የሥራ አፈጻጸም ደረጃ በደረጃ የተቀመጡ መሆናቸው በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሠ የተገለጸ ሲሆን ፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ፣ ለሌሎች አድባራት ደግሞ የምስክር ወረቀት ፣ አዲስ ተቋቁመው እያገለገሉ ላሉ አብያተ ክርስቲያናትም የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል። በልዩነት ደግሞ ለአድባራቱ አስተዳዳሪዎችና ሊቃነ መናብርት የምስጋና መርሐ ግብር ተደርጎ ተጠናቋል።

ምንጭ ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል

Share this post

Current News

1 min read

በደብራችን የግብረ ድቁና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አምስት ደቀመዛሙርት የድቁና ማዕረግ ተቀበሉ።

በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የግብረ ድቁና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አምስት ደቀመዛሙርት ኅዳር 21/2018 ዓ/ም በለንደን ጽርሐ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እጅ የድቁና ማዕረግ ተቀብለዋል።

Current News

1 min read

ዜና ቤተክርስቲያን

በዛሬው ዕለት በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያንየመጭውን የጻድቁ አባታችንን ዓመታዊ ክብረ በዓል በማስመልከት ለሚደረገው ዝግጅት በተለይ ቤተክርስቲያን ለመግዛት በሚደረገው ጥረት የህንጻ ግዢ የገቢ አሰባሳቢክፍሉ በደብሩ ያሉትን የአገልግሎት ክፍሎች በጋራ ሊያሳካ ስለሚችለው ውይይት አድርጏል ለዚሁም ይረዳው ዘንድ በዘመኑ ቴክኖሎጂን በመጠቅም ስልጠና ተሰጥቷል::

Current News

1 min read

ዜና ቤተክርስቲያን

በትናንትናው ዕለት ማለትም በ17/12/2017 ዓም (August 23/2025) በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አንድ አዲስ ነገር ተፈፅሟል ይኸውም ጀማል የተባለ ከእስልምና ወደ ክርስትና በመምጣት መስረታዊ የክርስትና ትምህርቱን በተገቢ መንገድ አጠናቅቆ የሥላሴ ልጅነቱን አግኝቷል ትምህርቱንም የሰጠው ዲያቆን ዘማርያም ሲሆን በደብራችንም ተጨማሪ ክትትል በማድረግ እነሆ ተከናውኗል እግዚአብሔር ይመስገን::