የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት የፍልሠተ ዐፅሙ መታሰቢያ በዓል
This post is only available in Amharic.
በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ቅዳሜ ግንቦት 9/2017 ዓ.ም ወይም May 17/2025 የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት የፍልሠተ ዐፅሙ መታሰቢያ በዓል ከጠዋቱ 5 AM ጀምሮ በድምቀት ይከበራል:: እርስዎም ቤተሰብዎም በስፍራው በመገኘት የበረከቱ ተካፋይ ይሁኑ።
13 Hardy St, Liverpool L1 5JN
St Vincent de Paul Catholic Church

"ፍልሰተ ዐፅም" የሚባለው የአንድ ሰው ዐፅም ከተቀበረበት የቀድሞ ስፍራው ተነስቶ (ፈልሶ)፥ ወደ ሌላ አዲስ ስፍራ ሲወሰድ ወይም ሲዘዋወር ነው፡፡
ስለዚህ "ፍልሰተ ዐፅሙ ለቅዱስ ተክለሃይማኖት" ማለት፥ ቅዱስ አፅማቸው ቀድሞ ካረፈበት (ከተቀበረበት) ስፍራ አሁን ወዳለበት መዘዋወሩን የሚያጠይቅ ነው፡፡ ብፁዓዊ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖት፥ የመጨረሻ ሕይወታቸውን ገድል በትሩፋት ጽሙድ ሆነው፥ በፍጹም ምናኔና ተባሕትዎ አሳልፈው፤ በጎ ዕረፍታቸውን ያረፉት፥ ሽማግሌው መነኩሴ፣ ትሑት አባት ተክለሃይማኖት፤ ፈጣሪኣቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በገባላቸው ቃል መሰረት፤ በኀምሳ ሰባት ዓመታት በኋላ፤ በመንፈሳዊ ልጆቻቸው አማካይነት፥ የተቀደሰ ዐፅማቸው ፈልሶ፥ ግንቦትግንቦት ፲፪ /12 ቀን ፲፫፻፶፪/1352 ዓ/ም አሁን ባለበት ቅዱስ ስፍራ ዐርፏል፡፡ ይህም ቅዱስ ዐፅማቸው የፈለሰበት ዕለት፥ "በዓለ ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለሃይማኖት" ተብሎ በየዓመቱ ይታሰባል፣ ይዘከራል፣ ይከበራል፡፡ የዮፍታሄ ልጅ፥ ሰውነቷ ለእግዚአብሔር ብፅዓት ሆኖ ተሰጥቶ ስለተሠዋች፤ እስራኤልም በየዓመቱ በኃዘን መታሰቢያዋን ያደርጉላት ነበር፡፡ መሳ ፲፩፥፴፬-፵/11፥30-40፡፡
እኛም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች፥ ከመምህሮቻችን በወረስነው ሥርዓት መሠረት፤ የሓዋርያው ተክለሃይማኖት "በዓለ ፍልሰተ ዐፅም" ፥ ግንቦት ዐሥራ ሁለት ቀን የቻልን ደብረ ሊባኖስ ተገኝተን፣ ያልቻልን ደግሞ፥ በኣቅራቢያችን ወዳለ ስማቸው ወደሚጠራበት ቤተክርስቲያን ሄደን እንዘክረዋለን፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎታችንም የሚያስነቅፈን አይደለም፡፡ በእምነት የሚደረግ ነገር ሁሉ፥ የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም፡፡
ለዚህ መረጃ (ምሳሌ) ካስፈለገን፥ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ፥ ወንድሞቹ ከግብፅ ምድር በሚወጡ ጊዜ፥ ዐፅሙን (የዮሴፍን) አፍልሰው ከእነርሱ ጋር የቃል ኪዳን ምድር ወደ ሆነችው ወደ ፍልስጥኤም ወስደው እንዲያሳርፉት መማጸኑን፤ ሙሴ ከጻፈው መጽሐፈ ኦሪት መመልከት ይቻላል፡፡ የቅዱሳን ‹‹ፍልሰተ ዐፅም›› ከዚህ ተያይዞ የመጣ ትውፊት ነው፥ ዘፍ ፶፥፳፬-፳፮/50፥24-26፣ ዘጸ ፲፫፥፲፱/13፥19፡፡ ዓለሙን አሸንፈው፣ አጋንንትን ድል ነስተው የኖሩ አግብርተ እግዚአብሔር ቅዱሳን፤ ከሥጋዊ ሕይወታቸው በኋላ ቅዱስ ዐፅማቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው፡፡ ለእኛም ለባርያዎቹ የእነርሱን በረከት ያደለን፣ ለዓለመ ዓለም አሜን፡፡
"ብዙህ ሕማሞሙ ለጻድቃን ወእምኲሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር፡፡ እግዚአብሔር የዓቅብ ኲሉ አዕፅምቲሆሙ ወኢይትቀጥቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ - የጻድቀን መከራቸው ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ከኣገኛቸው መከራ ያድናቸዋል፡፡ የቅዱሳንን ዐፅም እግዚአብሔር ይጠብቃል፡፡ ከዓፅማቸው አንድ ስንኳ አይጠፋም" መዝ ፴፫፥፳/33፥2 ብሎ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ፤ ቅዱሳን ከዕረፍታቸው በኋላ ዐፅማቸው ኃይለ እግዚአብሔር ይገለጽበታል፣ ገብረ ተአምራት ይፈጸምበጻል፡፡ በዓፅመ ቅዱሳን አማካይነት፥ በየጊዜው የሚፈጸመውን ተኣምር፥ ገድለ ቅዱሳን በየዘርፉ ይተርክልናል፡፡ ይህ በቅዱሳን ዐፅም አማካይነት የሚገለጽ የእግዚአብሔር ኃይል፤ ልብ ወለዳዊ ወይም ዐለማዊ ትረካ ሳይሆን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ አንድ ከዕብራዊ ወገን የሆነ ሰው ሞቶ፥ በኤልሳዕ ዐጽም አማካይነት ከሞት ተነሥቷል፥ 2ኛ ነገ ፲፫፥፳-፳፪/ 13፥20-22፡፡ የቅዱሳንን ዐፅማቸውን እንኳን ሳይቀር፥ በፍቅር ዐይን የምናየውና በአክብሮት የምንከባከበው፥ ፍልሰተ ዐፅም፣ ስባረ ዐፅም፣ ዝርወተ ዐፅም እያልን የምንዘክረው ስለዚህ ነው፡፡ (ዘፍ. 23፥1-17 ፤ 47፥29-30፤ 50፥24-26)፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገባም አራተኛ ዕጨጌ የሆኑት አባ ሕዝቅያስ፥ ይህንን አብነት ይዘው በዓፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ ሢመት ፲፫፻፵፬-፲፫፻፸፪ /1344-1372/ የኣቡነ ተክለሃይማኖትን ቅዱስ ዐፅም ከደብረ አስቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ እንዲፈልስ አድርገዋል፡፡ አባታችን ተክለሃይማኖት አስቀድሞ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ፥ ጌታችን ተገልጾ ቃልኪዳን በገባለቸው ጊዜ፥ "ሥጋዬ ይቀበር ዘንድ ወዴት ታዛለህ?" ብለው ሲጠይቁት "እስከ ኀምሳ ሰባት ዓመት ድረስ እዚህ ባረፍህበት ቦታ ይቆያል፡፡ በኋላ ግን፥ ይህች ዋሻ ትናዳለች፡፡
ልጆችህ በዚች ገዳም አደባባይ፥ ታላቅ ቤት በስምህ ሠርተው፥ የከበረ ሥጋህን አፍልሰው በውስጡ ያኖራሉ፡፡ በዚህ ቦታ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስም በቁርባንና በጸሎት ጊዜ፥ በላይዋ ይረባል፣ በውስጧም ደስታ ፍቅር ይሆናል" ብሎ መልሶላቸዋል፡፡(ገድለ ተክለሃይማኖት /ምዕራፍ ፬፥፲፯/ 4፥17)
በዓፅመ ኤልሳዕ አማካኝነት ተኣምራትን ያደረገ አምላክ፥ ዛሬም በኢትዮጵያዊው ኤልሳዕ በአቡነ ተክለሃይማኖት አፅም አማካኝነት፥ ድንቅ ሥራውን እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህም በዜና ተአምራቱ የተጠቀሰ ነው፡፡ ግንቦት ዐሥራ ሁለት ቀን፥ ዐሥራ ሁለት መምህራን ዋሻውን ከፍተው፤ የአባታችንን ቅዱስ ዐፅም በክብር ካወጡ በኋላ፥ ወደ ደብረ ሊባኖስ ቤተክርስቲያን አመጡት፡፡
ገብተው ሳንቃውን ይዘው ከሕዝብም ብዛት የተነሣ መብራት ጠፋ፡፡ ዐፅሙን ሦስት ጊዜ በመንበሩ አዞሩት፡፡ ብፁዓዊ አባታችን ተገለጡላቸው፡፡ የጠፋውም መብራት በራ፡፡ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ፊልጶስም ከአባታችን ጋር ነበሩ ቅዱስ ዐፅሙም (ሥጋውን) እስኪቀብሩ ድረስ በመንበሩ ላይ ተቀመጠ፡፡ የተሰበሰበውን ሕዝብ ሁሉ ባርከው በክብር ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ ከዚያም መምህራኑ በፍቅርና በደስታ ሆነው በዓሉን አክብረው ወደ በኣታቸው ተመለሱ፡፡
የጻድቁ አባታችን በረከታቸው ምልጃቸው በሁላችንም ላይ ይደር::
©ምንጭ፡- አውሎግሶን /ሕይወቱ ወገድሉ ለብፁዓዊ ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት/