Loading

ሰሙነ ሕማማት

This post is only available in Amharic.

“ሰሙነ ሕማማትን በፍጹም ጥንቃቄ ጠብቅ”
ሃይ.አበው ም 20፥19

የሰሙነ ሕማማት የጸሎትና የስግደት ሥነ ሥርዓት በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን

ከጠዋቱ 9am – 4pm

አድራሻ

ከሰኞ – ረቡዕ

Our Lady of the Annunciation
Bishop Eton Woolton Rd,
Liverpool L16 8NQ

ከሐሙስ – እሑድ

St Philip Neri Church
30 Catharines Street
Liverpool L8 7NL

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ከሆሳዕና በኋላ እስከ ትንሣኤ ድረስ ያሉ ቀናት ( አንድ ሳምንት) ወይም ከትንሣኤ በፊት ያሉት ቀናት (አንድ ሳምንት) ሰሙነ ሕማማት ተብሎ ይጠራል።ሰሙነ ሕማማት ማለት በአማርኛ የሕማማት ሳምንት ማለት ማለት ነው።

ሕማማት የሚለው ቃል ብዛት የሚያመለክት ሲሆን በነጠላ “ሐመ” ታመመ ካላው ግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው።ሕማም ሲባል ሰው ሰውኛውን ለእኛ የሚሰማንን ዐይነቱን የራስ ምታት የሆድ ቁርጠት እጅና የእግር ቁርጥማት አይደለም።ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ለማላቀቅ ከሲዖል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወዶ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራን የምናስብበት ነው።

ይሄውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል፦
ራሱን በዘንግ መመታቱን፣
በጥፊ ፊቱን መጸፋቱን፣
6666 ጊዜ መገረፉን፣
በጎዳና ላይ መውደቅ መነሣቱን፣
በመሬት ላይ መጎተቱን፣
ከምሰሶ ወደ ምሰሶ መንገላታቱን፣

ሐሞት መጠጣቱን፣
በቅንዋተ መስቀል መቸንከሩን
የምናስብበትና የምንዘክርበት ሳምንት ነው።
አባቶቻችንም ለዚህ ነው ይህን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ብለው የሰየሙት።ይህም ከላይ እንደተገለጸው፦
የመከራ ፣ የስቃይ እና የጭነቀት ሳምንት ማለት ነው።
በዚህ ሳምንት በዚህ ዓለም ለመኖር ሕይወታችን የሚጠይቁንን የዓለምን ለሳብ እና የዓለምን ምኞት ሁሉ ርግፍ አርገን ትተን በክርስቶስ ላይ የደረሱትን መከራና ስቃይ በሰሙነ ሕማማት (በሕማማት ሳምንት) እያሰብን በአንቅድዎ ልቡና እንጸልይ።

በሰሙነ ሕማማት የሚፈጸ ሥርዓቶች

1. ስግደት :-
በሰሙነ ሕማማት 41 ጊዜ ኪርያላይሶን 12 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት እየተዜመ እጅግ አብዝቶ ይሰገዳል።

2. ጸሎት :-
በሰሙነ ሕማማት ከ24 ሰዓት ውስጥ 10 የጸሎትና የንባብ ሰዓታት ይገኛሉ እነዚህም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ፣ 3 ሰዓት ፣ 6 ሰዓት ፣ 9 ሰዓት ፣ 11 ሰዓት እንዲሁም ከምሽቱ 1 ሰዓት ፣ 3 ሰዓት ፣ 6 ሰዓት ፣ 9 ሰዓት ፣ 11 ሰዓት ናቸው።

በእነዚህም ሰዓታት የጌታን ስቃይ ለማዘከር መዝሙረ ዳዊትና ግብረ ሕማማት ድርሳነ ማኅያዊ አብዝተው ይጸለያሉ።

3. ጾም :-
በሰሙነ ሕማማት ብዙ አዝማደ መባልዕት / አዘውትረን የምንመገባቸው ምግቦች አይበሉም። በዚህም ሳምንት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት እንድንጾም ይኸውም ቆሎ ፣ ዳቦ ፣ ወኃና ጨው ብቻ እንደታዘዙ በግብረ ሕማማት ላይ ተጽፎ ይገኛል።

በግብረ ሕማማት ውስጥ ወደ ግእዝም ሆነ በኋላ ወደ አማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የዕብራይስጥ፣ የቅብጥ እና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

ኪርያላይሶን፦

ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ «ኪርዬ ኤሌይሶን»ነው፡፡ «ኪርያ» ማለት «እግዝእትነ» ማለት ሲሆን «ኪርዬ» ማለት ደግሞ «እግዚኦ» ማለት ነው፡፡ ሲጠራም «ኪርዬ ኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡ ትርጉሙ «አቤቱ ማረን»ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ይኼውም ኪርዬ ከሚለው «ዬ» ኤላይሶን ከሚለው ደግሞ«ኤ» በመሳሳባቸው በአማርኛ «ያ»ን ፈጥረው ነው፡፡

ናይናን፦

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ፣ ማረን» ማለት ነው፡፡

እብኖዲ፦

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲ ናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው

ታኦስ፦

የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «ጌታ፣ አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡

ማስያስ፦

የዕብራይስጥ ቃል ሲሆነ ትርጉሙ «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው

ትስቡጣ፦

«ዴስፓታ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው

አምነስቲቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ፦

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ- አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ» ማለት ነው፡፡

አምንስቲቲ ሙዓግያ አንቲ ፋሲልያሱ፦

የቅብጥ ቃል ሲሆን «ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ -ቅዱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡

አምንስቲቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ፦

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡

የሰሙነ ሕማማት ዜማ

ከሰኞ እስከ ረቡዕ – ግዕዝ፣

ሐሙስ – አራራይ፣

ዓርብና ቅዳሜ – ዕዝል ነው፡፡

በእነኚኽ ዕለታት፣ ከኹሉም በፊት የሠዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል፡፡ የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፤ በዕለቱ ተረኛ መምህር /መሪጌታ / የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፡፡ ድጓው ከአራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋራ እንዲስማማ ኾኖ ነው የሚቃኘው፡፡ ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡ –
– ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
– ዐማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም
– ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም፤
– ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳዕየ እብል በአኮቴት አቡነ ዘበሰማያት

እየተባለ፣ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ ዐሥራ ኹለት ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡
ከዚያ በመቀጠል፡ –
✞ ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
✞ ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
✞ ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
✞ ለመንግሥቱ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም ዓለም
✞ ለሥልጣኑ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም ዓለም
✞ ለምኩናኑ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም ዓለም
✞ ለኢየሱስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም ዓለም
✞ ለክርስቶስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም ዓለም
✞ ለሕማሙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም ዓለም

✞ / በዓርብ ለመስቀሉ / ይደሉ
እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ ። በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ ይጀምራል። በመጨረሻ ተኣምረ ማርያም እና ተኣምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ፣” ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ “የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ፣ ምእመናንም፣ አቤቱ ይቅር በለን፤ እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡
ከዚያም ኹለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል። ዜማውን በቀኝ በግራ በመቀባበል፣ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል፡፡ እንዲኽ በማለት፡ –
ኪርያላይሶን / አምስት ጊዜ / በመሪ በኩል
ኪርያላይሶን / ሁለት ጊዜ / ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል
ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
ኪርያላይሶን ዐማኑኤል ናይን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን

በዚኽ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻ በግራ በቀኝ በማስተዛዘል 41 ጊዜ ይደገማል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት፣ የጌታችን ኅቡእ ስሞች ናቸው፡፡ ምንባባቱ ከመለያየታቸው በቀር በኹሉም ዕለታት ሥርዓቱ ተመሳሳይ ነው፡፡

Share this post

Current News

1 min read

በደብራችን የግብረ ድቁና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አምስት ደቀመዛሙርት የድቁና ማዕረግ ተቀበሉ።

በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የግብረ ድቁና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አምስት ደቀመዛሙርት ኅዳር 21/2018 ዓ/ም በለንደን ጽርሐ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እጅ የድቁና ማዕረግ ተቀብለዋል።

Current News

1 min read

ዜና ቤተክርስቲያን

በዛሬው ዕለት በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያንየመጭውን የጻድቁ አባታችንን ዓመታዊ ክብረ በዓል በማስመልከት ለሚደረገው ዝግጅት በተለይ ቤተክርስቲያን ለመግዛት በሚደረገው ጥረት የህንጻ ግዢ የገቢ አሰባሳቢክፍሉ በደብሩ ያሉትን የአገልግሎት ክፍሎች በጋራ ሊያሳካ ስለሚችለው ውይይት አድርጏል ለዚሁም ይረዳው ዘንድ በዘመኑ ቴክኖሎጂን በመጠቅም ስልጠና ተሰጥቷል::

Current News

1 min read

ዜና ቤተክርስቲያን

በትናንትናው ዕለት ማለትም በ17/12/2017 ዓም (August 23/2025) በሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አንድ አዲስ ነገር ተፈፅሟል ይኸውም ጀማል የተባለ ከእስልምና ወደ ክርስትና በመምጣት መስረታዊ የክርስትና ትምህርቱን በተገቢ መንገድ አጠናቅቆ የሥላሴ ልጅነቱን አግኝቷል ትምህርቱንም የሰጠው ዲያቆን ዘማርያም ሲሆን በደብራችንም ተጨማሪ ክትትል በማድረግ እነሆ ተከናውኗል እግዚአብሔር ይመስገን::