ሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዩኬና አየርላንድ ሀገረ ስብከት የሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በማኅበርነት ሰባት ዓመታትን ቆይቷል። በእነዚህ ሰባት ዓመታት ውስጥ ምእመናን የራሳቸው አገልግጋይ እና አጽናኝ ካህን ወይም መምህር ሳይኖሯቸው ከሌሎች ከተሞች በሚመጡ ካህናትና መምህራን በመጽናናት እግዚአብሔርን ዘወትር በማገልገል ቆይተዋል። ከሰባት ዓመታት በኋላ የምእመናኑ ጸሎት ተሰምቶ ልመናቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ አገልጋይ ካህን ካሉበት እግዚአብሔር ወደዚህ ሥፍራ አመጣቸው። ይህንን ፈቃደ እግዚአብሔር የተመለከቱት በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እንጦንስ አዲስ ከመጡት ካህን ቀሲስ ብርሃኑ ጋር በመነጋገር ቦታውን በቋሚነት እያገለገሉ ምእመናኑን እየባረኩ እና እያጽናኑ በእረኝነት እንዲጠብቁ አደረጉ። በዚህም መሠረት ቅዳሴ ቤቱ ጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም (Feb. 1 2014 GC) በብፁዕ አቡነ እንጦስ ተባረኮ የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ታቦት እንዲገባ የቦታውም ስም መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት እንዲባል ብሎም የካህኑ የማዕረግ ስም ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ብርሃኑ እንዲባል ተደረገ። ከዚች ዕለት ጀምሮ የሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሰፊ የሆነውን መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።