Liverpool M.K Abune Teklehaymanot Church
Ethiopian Orthodox Tewahdo Church In Liverpool

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 

ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንጮች እንደምንረዳው የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት የአይሁድ እምነት ገብቶ ለረጅም ዘመናት ቆይቷል፡፡ ከመረጃ ምንጮችም አንዱ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለችን” የሚለው ጥቅስ ነው/መዝ 67:31/

ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚናገሩ ሌሎች መረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ይገኛሉ:: እነዚህም በብሉይ ኪዳን ዘመን ኢትዮጵያውያን የእስራኤል አምላክ የሆነውን አንድ እግዚአብሔርን ያመልኩ እንደነበረ ያስረዳል:: ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለመረዳት ወደ ኢየሩሳሌም መሄዷና የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ኢትዮጵያ ከ982 ቅደመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የብሉይ ኪዳንን እምነት ተቀብላ እንደ ነበር በግልጽ ያሳያሉ:: /1ኛ ነገሥት 10:1-9/የብሉይ ኪዳን እምነት ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከኢየሩሳሌም ውጭ መስፋፋት እንደ ጀመረ ለክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ መግባት አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

በሠላሳ አራት /34/ ዓመተ ምሕረት ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ የነበረውና በወንጌላዊው ፊልጶስ የተጠመቀው የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ የገንዘብ ሚኒስትር ክርስትናን ለኢትዮጵያ አስተዋወቀ /የሐ.ሥ. 8:26-40/:: ይሁንና በመንበረ ጵጵስና ደረጃ የቤተ ክርስቲያን መመሥረትና ሥጋ ወደሙን ማቀበል የተጀመረው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ይኸውም ፍሬምናጦስ በእስክንድርያው ፓትርያርክ አትናቴዎስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ የተሾመበት 33ዐ ዓመተ ምሕረት ነበር፡፡ ፍሬምናጦስም ወንጌልን መስበክ ሲጀምር ወደ ክርስትና ሃይማኖት የመለሳቸው የመጀመሪያቹ አማኞች ያንጊዜ መንበረ መንግሥታቸውን በአክሱም አድርገው ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩት አብርሃ ወአጽብሐ ነበሩ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእስክንድርያን ቤተክርስቲያን ፈለግ በመከተል የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የኦርቶዶክስ እምነት ማዕከል ሆነች:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኬልቄዶንን ጉባኤ ከማይቀበሉት የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አቢያተ ክርስቲያናት አንዷ እንደመሆኗ

1) የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቱንና ሥራውን ተቀብላ በጥብቅ ትከታተላለች

2) በሐዋርያትም ሥራና ትምህርት ጸንታ ኖራለች! ትኖራለችም፡፡

3) ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያደረጓቸውን የሦስቱን ጉባያኤያት ውሳኔዎች ትቀበላለች፡፡ እነዚህም ጉባኤያት በ325 ዓ.ም የተደረገው የኒቅያ ጉባኤ ፣ በ381 ዓ.ም የተካሄደው የቁስጥንጥንያ ጉባኤና በ431 ዓ.ም የተደረገው የኤፌሶን ጉባኤ ናቸው፡፡ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ትምህርተ ሃይማኖት እነዚህ ሦስቱ ጉባኤያት ባሳለፉቸው ውሳኔች ላይ የተመሠረተ ነው::

በአራተኛውና በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመናት መካከል ያለው ጊዜ በቅዱስ ሰላማ /ፍሬምናጦስ/ እና በዘጠኙ ቅዱሳን ርዳታ ብሉያትና ሐዲሳት በግዕዝ ቋንቋ የተተረጐመበት፣ ገዳማት የተመሠረቱበት ጊዜ ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድም ቤተክርስቲያኒቱን እስከ አሁን ድረስ ከሌላው ሁሉ ለየት አድርጎ የሚያሳዩአትን ጸዋትወ ዜማን የደረሰውና ያዘጋጀው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ሆኖም በሰባተኛውና በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምና ሃይማኖት በቀይ ባሕር አካባቢ እየተስፋፋ መምጣቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቀረው የክርስትና ዓለም ጋር የነበራትን ግንኙነት እያደከመው መጣ:: በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመንም የአይሁድ እምነት ተከታይ የነበረችው የፈላሾች ንግሥት ዮዲት ተነስታ በአክሱምና በሌሎችም ቦታዎች በመስፋፋት ላይ በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ጥፋት ብታደርስም በ11ኛውና በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቢያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ሥራ ከፍተኛ እርምጃ ሊደረግ ችሏል:: ከፍልፍል ድንጋይ የተሠሩት የላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት የተገኙት በዚህ ዘመን ነበር፡፡ በ1270 ዓ.ም በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ታላቅ ጥረት ሥልጣን ከዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞን ሥርወ መንግሥት የተላለፈ ሲሆን ጻድቁ አባት ስላደረጉት ጥረትም ከሀገሪቱ ገቢ ሲሶው /1/3/ ለቤተክርስቲያኒቱ እንዲሰጥ ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጠንካራ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ተደርጎ የነበረ ሲሆን ከ1434 – 1468 ነግሠው የነበሩት አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለቤተ ክርስቲያኒቷ ሥርዓት መሻሻሎችን አድርገዋል::

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ሩብ ውስጥ ግራኝ መሐመድ ተነስቶ እጅግ በጣም ብዙ አቢያተ ክርስቲያናትን ሲያወድም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችንም አጥፍቷል፡፡ በዚህም ጊዜ ከመከራው ጽናት የተነሣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ እስልምና እምነት ቢገቡም ብዙቹ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ አማኞች ግን መከራውን በጽናት ተቋቁመው በኦርቶዶክስ እምነታቸው እንደ ጸኑ ኑረዋል፡፡ ይሁንና በኃያሉ እግዚአብሔር ርዳታ ያንጊዜ ከፖርቹጋል መንግሥት ተልከዉ በመጡ ወታደሮች ድጋፍ ከ15 ዓመታት ጥፋት በኋላ ግራኝ መሐመድ ድል ሆኗል:: ከዚህ ድል ቢኋላም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ሱስንዮስ አማካይነት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ተሞክሮ የነበረው የካቶሊክ እምነትም እንደተሞከረው ሳይሆን ቀርቶ በብዙ መሥዋዕትነት የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ እምነትና ሥርዓት ጸንቶ ሊኖር ችሏል:: በ18ኛውና በ19ኛው ምዕት ዓመታትም የሀገራችን አንድነት በመሳፍንት አገዛዝ የመከፋፈል ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ የሀገሪቱ አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር የሚያስችል ታላቅ ድርሻ አበርክታለች። ይህም ሁኔታ ቤተክርስቲያኒቱ በሕዝቡ ዘንድ የአንድነትና የኔነት ምልክት ሆና እንድትታይ አድርጓታል፡፡ አፄ ቴድሮስ በ1855 ዓ.ም መንግሥታዊ ሥልጣን በጨበጡ ጊዜ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ ያነሣሣቸው ዋናው ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ ተይዞ የቆየው የአንድነት መንፈስ ነው::  በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን /1920 – 1967 መጀመሪያ/ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ከግብጽ ቤተክርስቲያን ቀኖናዊ አገዛዝ ተላቃ ነፃነቷን እንድታገኝ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል:: በመሆኑም ከ1921 ዓ.ምጀምሮ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ከሊቃውንቶቿ መካከል እየመረጠች ጳጳሳትን እንድትሾምና በእነሱ አመራር እንድትተዳደር ተደርጓል:: የመጀመሪያውም ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በ1951 ዓ.ም ለመሾም በቅተዋል:: 

በአሁኑ ጊዜ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በ6ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አመራር በቅዱስ ሲኖዶስ እየተዳደረች ትገኛለች፡፡ በዚህም አመራር የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ማኀበራዊ አገልግሎት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገርም በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቤተክርስቲያኒቷን አገልግሎት ለማጠናከር  እና አንድነቷን ለመጠበቅ ከፍተኛ ቁርጠኝነት የተመላው ርምጃ አሳይተዋል፡፡