Liverpool M.K Abune Teklehaymanot Church
Ethiopian Orthodox Tewahdo Church In Liverpool

የዐቢይ ጾም ሶስተኛው ሳምንት – ምኵራብ / Temple

በዕለቱ የሚነበቡት መልዕክታት

የጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆላስያስ ሰዎች:- ም. 2 ቊ. 16-ፍ.ም
St Paul’s letter to the people of Colossians:- ch. 2 nu. 16-end
የያዕቆብ መልዕክት:- ም. 2 ቊ. 14-ፍ.ም
St James’s letter:- ch. 2 nu. 14-end
የሐዋርያት ሥራ:- ም. 10 ቊ. 1-9
Acts of The Apostles:- ch. 10 nu. 10-9

ምስባክ

እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ።
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ።
ወቀፃዕክዋ በጾም ለነፍስየ።
መዝሙር:- ፷፰: ፱-፲

የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና።
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት።
መዝሙር:- 69:9-10

For the zeal of thine house hath eaten me up;
and the reproaches of them that reproached thee are fallen upon me.
I chastened my soul with fasting.
Psalms:- 69:9-10

ወንጌል / Gospel

ዮሐንስ:- ም. ፪(2) ቊ. ፲፪(12)-ፍ.ም
John:- ch. 2 nu. 12-end

ቅዳሴ / Liturgy

ሦስተኛው ሰንበት “ምኲራብ” ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት “ቦአ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ” ነው፣ ምኩራብ ማለትም ቀጥተኛ ፍችው ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ህንፃ ማለት ነው፣ ከዚህም የተነሣ “የአይሁድ ቤተ ጸሎት ወይም ቤተመቅደስ” ማለት ይሆናል፣ ዐቢይ ፍሬ ቃሉ ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በትምህርቱ፣ ድውያነ ነፍስን በታምራቱ ሲፈውስ በምኩራብ ዮሐንስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 12 እየተገኘ የፈጸመውን የማዳን ሥራ በኀሊና እያሳሰበ የሚያስተምር ሦስተኛ ሳምንት ነው፡፡

ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኲራብ ገባ እያለ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሳሳ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኲራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኲራብ የሚሸጡ፣ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ፣ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፣ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ቁጥር 12-13 ተጠቅሷል፡፡

ቆላስያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 16-23 “እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል፣ ወይም ስለ ወር መባቻ፣ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፣ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፣ ትህትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሠሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡

ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት “አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ” ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፣ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን”ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም” ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣
ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጧቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ፣ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡

በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፣ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሐም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም አብርሐምም እግዚአብሔርን አመነ፣ ፅድቅም ሆኖ ተቆጠረለት ያለው ተፈፀመ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፣ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲፀድቅ ታያላችሁ”፣ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ፣ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው”

የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ቁጥር 1-9 “በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፣ እርሱም ፅድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ፣ ለህዝብም ብዙ ምፅዋት የሚያደርግ፣ዘወትር  ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፣ እግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት  “ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው” እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ “ጌታ ሆይ ምንድን ነው? አለ፣ መልአኩም  “ጸሎትህና ምፅዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረጓል” አለው፣ አሁንም “ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፣ እርሱ ቤቱ በባህር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጧል፣ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፣ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፣ እነርሱም በነጋታው ሲሄዱ፣ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ፣ መዝሙር ምዕራፍ 68 ቁጥር 9-10 የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና ሰውነቴን በጾም አደከምኳት፣ ስድብንም ሆነብኝ”፡፡

ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ “ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ”፣ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፣ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፣  ዮሐንስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 12 -25 ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፣ ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፣ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፣ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” አላቸው፣ ደቀ መዛሙርቱም “የቤትህ ቅናት ይበላኛል” ተብሎ እንደተፃፈ አሰቡ፡፡

ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት፣ ኢየሱስም መልሶ “ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው” ስለዚህ  አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት፣ እርሱ ግን “ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር” ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡

በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ “ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና”

“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”

ምንጭ ዮሐንስ ንስሐ የቴሌግራም ግሩፕ
https://t.me/+ReLdpifiso4Sz04q

Leave a comment