የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት መጠናቀቁን አስመልክቶ፤ በዛሬው ዕለት በደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ በዓመቱ የተሠሩት ሥራዎች እና የተገኘው አመርቂ ውጤት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን ለብፁዕነታቸው እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ መስተዳደር ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና ቀርቧል። በተያያዘም በክፍለ ከተማው የሚገኙ አድባራት እርስ በእርስ ተግባብተውና ተነጋግረው ስለሚሠሩ የሚሰጠው አገልግሎት እየሰፋ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ፣ ለምእመኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ቤተ እምነቶች ጭምር ወደ ክርስትና መመለስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ፣ የጠቅላይ ቤ/ክ እና የአ/አ/ሀ/ ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም በክፍለ ከተማው ስር ባሉ አድባራትና ገዳማት የሚያገለግሉ አስተዳዳሪዎች፣ፀሓፍት፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት፣ የሂሳብ ሹሞች፣ቁጥጥሮች፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ፍሬ ጻማከ ተሴሰይ ብፁዕ አንተ ወሰናይ ለከ ። መዝ 128፥2” ላይ የሚገኘውን ኃይለ ቃል በማንሳት የተዘጋጀውን የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር በማመስገን “ይህ ሽልማትና ዕውቅና የሚገባው የአዝመራው የእሸቱ ፍሬ ለሆኑት ዓመቱን ሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ማኅሌቱን ፣ ሰዓታቱን ያለማቋረጥ ሲያገለግሉ ለነበሩ ሊቃውንት ፣ ካህናት ነው ።” በመቀጠልም ምእመናን በሰላም አገልግሎት እንዲያገኙ ላስቻሉ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን ፣ በክፍለ ከተማው ስለሚታየው የስብከተ ወንጌል መስፋፋት ፣ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሠ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅን አመሥግነዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም በሀገረ ስብከቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉንም ሠራተኛ በማሰልጠን የማብቃት ሥራ መሠራት እንዳለበት አንስተው ሥልጠናዎች ከሀገረ ስብከት እስከ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በማሳሰብ በቀጣዩ ዓመት ሁሉም አገልጋይ ቤተ ክርስቲያን የጣለችበትን ኃላፊነት አጠናክሮ መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው በዚህ ዓመት የሰበካ ጉባኤ ሕግን የማወቅና የማስፈጸም ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ይዞታ የማስፋፋት ፣ ያሉትን ይዞታ የማስጠበቅ ሁኔታ የታየበት ነው ፤ ይሄ ሁሉ ስኬት የተገኘው ሥራው የሀገረ ስብከቱ ብቻ ነው ሳይሉ በራሳቸው ጥረት ብዙ በመሥራታቸው ነው ፤ ይሄ ሽልማት በቀጣይ የተሻለ እንዲሠሩ ማበረታቻ ይሆናል ባማለት መርሐ ግብሩን ያዘጋጁ ባለ ድርሻ አካላትን አመሥግነዋል።
የሽልማት ሒደቱን በተመለከተ በተለያየ መስፈርት እና የሥራ አፈጻጸም ደረጃ በደረጃ የተቀመጡ መሆናቸው በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሠ የተገለጸ ሲሆን ፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ፣ ለሌሎች አድባራት ደግሞ የምስክር ወረቀት ፣ አዲስ ተቋቁመው እያገለገሉ ላሉ አብያተ ክርስቲያናትም የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል። በልዩነት ደግሞ ለአድባራቱ አስተዳዳሪዎችና ሊቃነ መናብርት የምስጋና መርሐ ግብር ተደርጎ ተጠናቋል።
ምንጭ ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል
